ቀጥታ፡

ለዋናው የምክክር ጉባኤ የተዘጋጁ አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው - ምሁራን

አዲስ አበባ፣ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተለይተው ለዋናው የምክክር ጉባኤ የቀረቡ ስምንቱ አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ፡፡    

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዋናውን የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ ማካሄዱ ይታወቃል፡፡    

በዚህም ከመጭው ሀምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚያካሂደው የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ ስምንት አጀንዳዎች ለይቶ አቅርቧል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህርና ተመራማሪ  ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤  በምክክር ሂደቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸው ኮሚሽኑ የአካታችነት መርህን መከተሉን  አመላካች ነው ብለዋል።

ምክክሩ የታጠቁ ቡድኖች ጭምር ወደ ሰላም በመምጣት የተሳተፉበት መሆኑን አስታውሰው፤ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የሚያስችል ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መሠረታዊ የሆኑ የልዩነት ሀገራዊ ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በምክክር ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ምቹ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

በወሳኝ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠርም ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

በኮሚሽኑ ለዋናው ጉባኤ ተለይተው የቀረቡ አጀንዳዎች ተቃርኖዎችን ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲፈቱ መሰረት የሚጥሉ ናቸው ብለዋል።

ዶክተር ሙሉጌታ አክለውም ሂደቱ በግጭት የሚታወቀውን የታሪክ ምዕራፍ በመቀየር፤ በኢኮኖሚዋ የበለጸገች፣ በጂኦ-ፖለቲካና በጂኦ-ስትራቴጂ ረገድ ጠንካራ የሆነች ሀገር ለመገንባት መሰረት ይጥላል ብለዋል።  

የኢትዮጵያን ተመራጭነት ከፍ ወዳለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ያሉት ምሁሩ፥ ሁለንተናዊ ሰላም የሰፈነባትና በቀጣናው ያላትን ሚና አጠናክራ እንድትቀጥል አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል። 


 

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የሥነ-መንግሥት አስተዳደር እና የሕዝብ አስተዳደር ተመራማሪና ተንታኝ ጫሊ ኢተፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኮሚሽኑ የቀረቡ የምክክር አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡    

በኮሚሽኑ የቀረቡት አጀንዳዎች እንደ ሀገር በሰለጠነ መልኩ የመመካከር ልምድ እንዲዳብር የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ወደ ጋራ አሸናፊነት የሚያመጣ መንገድ ነው ብለዋል።

የሀገረ መንግሥት ግንባታ፤የመንግሥት አደረጃጀት እና ቅርጽ፣የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌደራል ከተሞች (የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እና የድሬዳዋ አሥተዳደር) ጉዳይ፤ የሐይማኖት ጉዳዮች፤ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት ለዋናው ጉባኤ ከተለዩ አጀንዳዎች መካከል ናቸው።

ሰብዓዊ መብቶች ፣ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ፣የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፤ሙስና እና መልካም አሥተዳደር  እንዲሁም የሰላም ግንባታ ጉዳዮችንም ውይይት የሚደረግባቸው አንኳር ነጥቦች መሆናቸውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም