ቀጥታ፡

ከለውጡ ወዲህ ለስፖርት ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል

አዳማ ፤ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ) ፡-ከለውጡ ወዲህ ለስፖርት ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

11ኛው ዓመታዊ የኢትዮጵያ ስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባዔ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ ሙሐመድ እንደገለፁት፤ ከለውጡ ወዲህ ለስፖርት ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል። 

የዘርፉን ሪፎርም ለማሳካት የስፖርት ስርዓት ግንባታ፣ አደረጃጀት፣ ህግና አሰራርን ማዘመን እንዲሁም በዘርፉ የግሉን ሴክተር ተሳትፎ ማጠናከር ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተለይም የስፖርት ልማት ፖሊሲን ጨምሮ የስፖርት ልማትና አስተዳደር አዋጅን ከማውጣት ባለፈ፣ አሰራሮችና ደንቦችን ለመከለስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዚህም የስልጠና ጣቢያዎችና ማዕከላት ያሉባቸውን ችግሮች በመቅረፍ በአዲስ መልክ ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰው፤ ታዳጊዎችን ጨምሮ ከ40 ሺህ በላይ ሰልጣኞች በስልጠና ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከለውጡ ወዲህ ከ130 ሺህ በላይ የስፖርት አደረጃጀቶች መፈጠራቸውን የገለፁት አቶ መኪዩ፤ ቀደም ሲል የነበረውን 27 ሺህ 539 የስፖርት መሰረተ ልማት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ወደ 45 ሺህ 871 ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል። 

ከእነዚህም ውስጥ 43 ሺህ 335 የሚሆኑት የስፖርት ማዘውተሪያዎች ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያገኙ መሆናቸውን አብራርተዋል። 

በተመሳሳይም ደረጃቸውን የጠበቁና ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የሚያሟሉ ስታዲየሞች በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳርና በሐዋሳ ከተሞች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዘርፉን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሻገር የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አካዳሚው የምርምር ውጤቶችን በግብዓትነት ከማቅረብ ባለፈ፣ የማማከር ስራውን በማጠናከር የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው በበኩላቸው፤ አካዳሚው የስፖርት መሰረተ ልማት ማነቆዎችን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን በጥናትና ምርምር እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 


 

የማሰልጠኛ ተቋማትን ማስፋፋትና የስፖርት ሙያተኞችን ማፍራት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በአደረጃጀት፣ በስልጠና፣ በምልመላ፣ በውድድርና በተቋማዊ ለውጥ ላይ የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር እየቀየረ ነው ብለዋል።

አካዳሚው የስፖርት ፌዴሬሽኖችን፣ ክልሎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የማማከር ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባዔ ላይ 12 የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም