ቀጥታ፡

ከአየር ትንበያው መረጃ በመነሳት ጉዳት እንዳይደርስ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል-ኢንስቲትዩቱ

ሰመራ፣ሰኔ 25/2018(ኢዜአ)፦ከአየር ትንበያው መረጃ በመነሳት ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለማስቀረት፣የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን በትኩረት ማከናወን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስገነዘበ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የ2018 ዓ.ም የአፋር ክልል የአየር ንብረት እይታን በተመለከተ "ከትንበያ ወደ ተግባር" በሚል መሪ ሐሳብ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የአፋር ክልል በአብዛኛው በደጋማ አካባቢዎች በሚጥለው ዝናብ ምክንያት ለሚከሰት ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ እና በሌላ በኩል ደግሞ ለረጅም ጊዜ ለሚዘልቅ ድርቅ ተጋላጭ ከሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት "ከትንበያ ወደ ተግባር" በሚል መሪ ሐሳብ የሚያዘጋጃቸው እነዚህ መድረኮች፣ ቀደም ሲል ይደረጉ ከነበሩ የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን በቀላሉ የማሳወቅ ልማድ ባለፈ፤መረጃዎቹን በቀጥታ መሬት ላይ ካሉ የቅድመ ጥንቃቄ እና የዕለት ተዕለት የልማት ሥራዎች ጋር ለማቀናጀት ያለሙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ጠባይ ለውጥ አመራር ሥራ አስፈጻሚ ጫሊ ደበሌ በዚሁ ወቅት፤በአፋር ክልል የዘንድሮው የክረምት ዝናብ ስርጭት ከመደበኛው በታች ሊሆን እንደሚችል የአየር ትንበያ መረጃዎች ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት የግብርና፣የውኃ፣የአደጋ መከላከልና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የትንበያ መረጃውን መሠረት በማድረግ፣ ከወዲሁ የተለዩ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአፋር ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ቱሊ በበኩላቸው፤በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአርብቶ አደር አካባቢዎች የውኃ እጥረት እንዳያጋጥም የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

መረጃዎችን በአግባቡና በየወቅቱ ለሚመለከታቸው አካላት በማድረስ፣ኅብረተሰቡ የአደጋ ሰለባ እንዳይሆንና ሀብቱን እንዳያጣ ከወዲሁ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ የራሱን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚተላለፉ መረጃዎችን በንቃት መከታተል እንደሚገባው አብራርተዋል።

በአፋር አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ማሄ ዓሊ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የክረምት ወቅት የትንበያ መረጃውን መሠረት በማድረግ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚገኙበት ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጸዋል።

በተሰጠው የትንበያ መረጃ መሠረት በክልሉ በሚገኙ 21 ወረዳዎችና 173 ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ 150 ሺህ ሰዎችን ታሳቢ በማድረግ፣ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ግብረ ኃይሉ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን እንደሚያከናውንም አስረድተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከተለያዩ የሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ወረዳዎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም