በግብርናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮች መዘርጋታቸው ከተረጂነት ለመውጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
በግብርናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮች መዘርጋታቸው ከተረጂነት ለመውጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል
ጅማ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):-ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮች መዘርጋታቸው ከተረጂነት ለመውጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ያግዘዋል ሲሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቴክኖሎጂና ግብዓት በወቅቱ የተሟላለት የግብርና ስራ ምርታማ በመሆኑም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ከተረጂነት ለመውጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ያፋጥናል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ባለሙያ እና ተመራማሪ አደባ ገመቹ (ዶ/ር)፤ ግብርናው በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ ምርታማነትን እያሳደገ መጥቷል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት መንግሥት በሁሉም እንቅስቃሴዎቹ የባለሙያዎችን እና የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱንም አስታውሰዋል።
በዲጂታል ግብርና ትግበራ አርሶ አደሩ መሬት ለማዘጋጀትና ዘር ለመዝራት መጠቀም ያለበትን ትክክለኛ ጊዜን ጨምሮ፣ ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን እንዲያገኝ መደረጉ የምርታማነት ዕድገት ጥረቱን ወደ ተጨባጭ ውጤት እየቀየረው መሆኑን ገልጸዋል።
ለአርሶ አደሮች የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ እንዲደርስ መደረጉም ለተገኘው ውጤት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
በዚህም ግብርናውን ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ በመስኖና በሌሎች አማራጮች በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ ማልማት፣ የአርሶ አደሩን ሕይወት ከማሻሻል ባለፈ ከተረጂነት ለመውጣት እንደሚቻል አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም የገበያ ትስስርን በመፍጠር፤ የኮንትራት እርሻን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ምርት የሚረከቡ ተቋማትና ፋብሪካዎች መፈጠራቸው በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።
በዩኒቨርሲቲው የግብርናና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ ዲን፣ የአፈር ልማት፣ የሰብል እንክብካቤና ንጥረ-ነገር ባለሙያ ሰለሞን ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ምርታማነትን በማላቅ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
በዚህም የፍራፍሬና የቅባት እህሎች በስፋት ከመመረታቸውም በላይ ምርቶቹን የሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች መቋቋማቸውን ጠቁመዋል።
በቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርትን በአግባቡ መሰብሰብ በመቻሉም የብክነት መጠን ቀንሶ ምርታማነት መጨመር መቻሉንም አክለዋል።
እንዲሁም መንግሥት ዘመናዊ የግብዓት ማቆያና ማከማቻ ሥፍራዎችን አዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረጉና ሰፊ ግንዛቤ መፍጠሩ በዘርፉ የታየ ሌላኛው ትልቅ የለውጥ ምዕራፍ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከዚህም ባሻገር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትለው ችግር በመከላከል ረገድ ለግብርናው ዘርፍ በጎ ሁኔታ መፍጠሩንም አመልክተዋል።
ወጣቶችን በግብርና በማሳተፍ፣ የአፈር ጥበቃ ሥራዎችን በማጎልበትና የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሳለጥ ረገድ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ለስኬቱ አጋዥ መሆኑንም አብራርተዋል።
መሰል ሥራዎች ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆናቸውን ጠቁመው የሚፈለገው ግብ ላይ ለመድረስ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል ብለዋል።