ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡት አጀንዳዎች ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት መሰረት የሚጥሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡት አጀንዳዎች ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት መሰረት የሚጥሉ ናቸው
ሀዋሳ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የለያቸው የምክክር አጀንዳዎች ጠንካራ ሀገረ መንግስትን ለመገንባት የሚያስችሉ መሆናቸውን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
አጀንዳዎቹ ለዘመናት የቅራኔ ምንጭ የሆኑ ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት ጽኑ ሀገር ለመገንባት የሚያስችሉ አስተማማኝ መሠረቶች እንደሆኑም ምሁራኑ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችን በሀገራዊ ምክክር በመፍታት ጠንካራ ሀገረመንግሥት ለመገንባት በምክክር ኮሚሽን የተጀመረው ጥረት በየደረጃው ተካሂዶ መጨረሻው ምዕራፍ የምክክር አጀንዳዎች ለህዝብ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
የአጀንዳዎቹን አሳታፊነትና የህዝቡን ሚና አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳሉት፤ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የዜጎች ሁለንተናዊ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በኮሚሽኑ የተለዩት አጀንዳዎች የሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎት ያማከሉ በመሆናቸው አለመግባባቶችን በውይይት ፈትቶ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊና ስነሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ የለያቸው አጀንዳዎች ተቃርኖዎችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት መሰረት የሚጥሉ ናቸው።
እንደሀገር ለአለመግባባት ምክንያት የሆኑና ለዘመናት የቆዩ ችግሮች እንዳሉ አስታውሰው፣ በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ልዩነትና ቅራኔ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የውይይት አጀንዳዎችን ለማሰባሰብ በየደረጃው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባወያየበት ወቅት የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ወክለው መሳተፋቸውንም እንዳልካቸው (ዶ/ር) አንስተዋል።
ኮሚሽኑ በአሳታፊነት ከህዝብ ያሰባሰባቸውን አጀንዳዎች በጥንቃቄና የሁሉን ፍላጎት ባካተተ መልኩ አደራጅቶ ለማጠቃለያ ምዕራፍ ማቅረቡ ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።
የማጠቃላያ ጉባኤው ስኬታማ እንዲሆንም ሁሉም ታሪካዊ እድሉን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ገልጸው፣ ለዚህም ከራስና ከቡድን ፍላጎት ይልቅ ሀገርን በማሰብና በማስቀደም ልዩነትን ማጥበብና ማቻቻል ያስፈልጋል ብለዋል።
ኮሚሽኑ የለያቸው የምክክር አጀንዳዎች ሀገርን የሚያሻግሩና የሚያጸኑ ናቸው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ብሩክ ደስታ ናቸው።
በአጀንዳዎቹ ላይ በስክነትና በቅንነት በመወያየት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በሀገራዊ ምክክሩ ድርሻቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
በንግግር ልዩነቶችን መፍታት የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ ነው ያሉት መምህር ብሩክ፣ አሁን የተፈጠረውን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን መክረዋል።
በኮሚሽኑ የቀረቡ አጀንዳዎችን ከውጤት በማድረስ የጋራ ትርክትና ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ የሁሉንም የነቃ ተሳትፎ እንደሚፈልግም አንስተዋል።
በመሆኑም ሁሉም በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል፤ የእኔም አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው የሚል አስተሳሰብ በመያዝ ለምክክሩ ስኬት እገዛውን እንዲያደርግም አመልክተዋል።