የንግድ ባዛሩ ለአምራቾች ምርትን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስስር እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የንግድ ባዛሩ ለአምራቾች ምርትን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስስር እየፈጠረ ነው
ወልቂጤ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):-በወልቂጤ ከተማ የተከፈተው የንግድ ባዛርና አውደ ርዕይ ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅና ከመሸጥ ባለፈ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እያገዛቸው መሆኑን አምራቾችና ኢንተርፕራይዞች ገለጹ።
ለሦስት ቀናት በሚካሄደው አውደ ርዕይ እና ባዛር ላይ ከ120 በላይ አምራቾች የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የእደ ጥበብ ምርቶችን ይዘው ቀርበዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አምራቾችና ኢንተርፕራይዞች እንዳሉት አውደ ርዕዩና ባዛሩ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ እንዲሁም ለቀጣይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከባዛሩ እና አውደርዕዩ ተሳታፊዎች መካከል የዳሪም ዱቄት ፋብሪካ የሰው ሃብትና ንብረት አስተዳደር ማናጀር አቶ ወንድምአገኝ ታሪኩ፣ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ይዘው መቅረባቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች በተዘጋጁ ባዛርና አውደ ርዕይ ላይ ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸው፣ ይህም የገበያ ዕድልን ለማስፋትና ደንበኛ ለማፍራት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ከወልቂጤ ማረሚያ ተቋም የተለያዩ የእደ ጥበብ ውጤቶች ይዘው በባዛሩ ላይ የተሳተፉት አቶ አብድልከሪም ጀማል በበኩላቸው፤ በባዛሩ የተፈጠረላቸው የገበያ ዕድል ምርቶቻቸውን በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ማረሚያ ተቋሙ ታራሚዎችን በስነ ምግባር ከማነጽ ባለፈ የተለያየ ሙያ ባለቤት እንዳደረጋቸው ገልጸው፣ በኢንተርፕራይዝ በማደራጀት ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የንግድ ባዘሩና አውደ ርዕዩ አምራቹን ከሸማቹ ማህበረሰብ ጋር በማገናኘት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፍኸር ጨርቃጨርቅ ማኑፋክቸሪንግ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ዚኪራ ሙራድ ናቸው።
ኢንተርፕራይዞች እርስ በርስ ልምድ ከመለዋወጥ ባለፈ የገበያ ዕድል ለማግኘት ማስቻሉን ገልጸው፣ በባዛሩ ከሌሎች ጋር የገበያ ትስስር እየፈጠሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
በባዛሩ ላይ ግብይት ሲፈጽሙ የነበሩት የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሪት አሰለፈች አህመድ በበኩላቸው፤ የእደ ጥበብ ውጤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የሚዘጋጁ ባዛርና አውደርዕዮች ሸማቹን ከአምራቹ ጋር ስለሚያገናኙ ሁለቱንም ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት ነዋሪዋ፣ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በወልቂጤ ከተማ ለሦስት ቀናት በተዘጋጀው የንግድ ባዛርና አውደ ርዕይ ከ120 በላይ አምራቾች የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የእደ ጥበብ ውጤቶችን ይዘው ቀርበዋል ያሉት ደግሞ የጉራጌ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙራድ ያሲን ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት ባዛር እና አውደርዕዩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ልምድ ለመለዋወጥ እና የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ ነው።