በሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ቅርሶችን በመታደግ የሐረርን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻነት እያጎለበቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ቅርሶችን በመታደግ የሐረርን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻነት እያጎለበቱ ነው
ሐረር፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ቅርሶችን በመታደግ የሐረርን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻነት ማጎልበቱን የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ገለጸ።
መንግሥት ያዘጋጀው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብር ከለያቸው አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው።
ከዚህ ቀደም ዘርፉ በበቂ ሁኔታ ሳይለማና የገቢ ምንጭነቱ ሳይጎለብት በመቆየቱ፣ አሁን ላይ ሀገራዊ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደ ዋና ሞተር ተለይቶ እየተሰራበት ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ቱሪዝም አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር!” በሚል በሰጡት ማብራሪያም በዘርፉ ልማት የተከናወኑ ተግባራትንና የመጡ ውጤቶችን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ የብዝሃ የኢኮኖሚ አማራጮችን መሰረት አድርጎ በመስራት በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት በማሳያ አስቀምጠዋል።
የጥንት ውበታቸውን ከዘመናዊ ገጽታ ጋር በማሰናሰል የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ በለውጡ መንግሥት እንደ አዲስ ከተገነቡና ከተሻሻሉ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የሐረር ከተማ ቀዳሚዋ ነች።
የሐረር ጀጎል ግንብና በውስጡ የሚገኙት ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሀብት መሆናቸው ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማትና የቅርሶች እድሳት ስራ፣ የታሪካዊቷን ሐረር ከተማ የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ በማነቃቃት ለአካባቢያዊና ሀገራዊ ኢኮኖሚው አዲስ አቅም እየፈጠረ ይገኛል።
የክልሉ የቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ እንደገለጹት፣ በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና እምቅ አቅሙን ለመጠቀም መጠነ-ሰፊ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
የቱሪዝም ዘርፉን ለማጎልበት የተከናወኑት ተግባራትም ለአደጋ ተጋርጠው የነበሩ ቅርሶች እንዲለሙና ይዘታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማስቻላቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸው፤ ይህም ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
በዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የቱሪዝም መስህቦችን በማልማት፣ የጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘምና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ አቅም በማሳደግ ረገድ የተሻሉ ተግባራት የተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮ ዓመት ክልሉን የጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ካለፈው ዓመት የ47 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ይህም መሠረተ-ልማቶች ሲሟሉ የቱሪዝም ዘርፉ የኢኮኖሚው ዋነኛ ምሰሶ እንደሚሆን አመላካች ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሳሚ ገለጻ፣ የቱሪዝም ዘርፉን ለማጎልበት የተከናወኑት ተግባራት ከውጭ ሀገር ቱሪስቶች ባሻገር የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችና ሌሎች አካላት ሐረርን እንዲጎበኙና ውበቷን ለዓለም እንዲያስተዋውቁ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።