በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው ክረምት በ100 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ በኩታ ገጠም ይተከላል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው ክረምት በ100 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ በኩታ ገጠም ይተከላል
ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):-በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው ክረምት በ100 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ በኩታ ገጠም እንደሚተከል የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ተሾመ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለቡና ልማት ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በዞኑ በያዝነው ክረምት በቡና ከሚለማው አጠቃላይ ከ320 ሄክታር መሬት ውስጥ ከ100 ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም የሚለማ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በበጋው ወቅት ከተዘጋጀው ከ916 ሺህ በላይ የቡና ችግኝ ውስጥም ከ330 ሺህ በላይ የሚሆነው ለኩታ ገጠም ልማት እንደሚውል ተናግረዋል።
የቡና ኩታ ገጠም ልማቱ የሚካሄደውም ተስማሚ ስነ ምህዳርና የአየር ንብረት ባላቸው በደብረ ኤሊያስ፣ በማቻከልና ጎዛምን ወረዳዎች መሆኑን አመላክተዋል።
በዞኑ በሚካሄደው የቡና ልማትም ከ690 በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በዞኑ የጎዛምን ወረዳ የሊባኖስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ክብረት በዛበህ ፤ በተያዘው ዓመት ቡናን በኩታ ገጠም መትከል መጀመራቸውን ነው የሚናገሩት።
ከዚህ በፊት ቡናን በጓሯቸው በማልማት ለቤት ውስጥ ፍጆታ ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅም ከግማሽ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት ላይ ቡናን በኩታገጠም በማልማት ለገበያ ለማቅረብ እየሰራሁ ነው ብለዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መንግስቱ ክፍሌ በበኩላቸው እንደሌሎች ሰብሎች ቡናን በኩታ ገጠም ለማልማት ከግማሽ ሄክታር በላይ መሬት በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም የማሳ ዝግጅት በማጠናቀቅ በጋራ የሚተከልበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።