ቀጥታ፡

ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የተመረጡት ስምንቱ አጀንዳዎች ስር የሰደዱ ችግሮችን በጥልቀት ለመመካከርና ለመፍታት የሚያስችሉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):-ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የተለዩት ስምንት አጀንዳዎች የሀገሪቷ ስር የሰደዱና የቆዩ ችግሮች ላይ በጥልቀት ለመመካከርና ለመፍታት የሚያስችሉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰኔ 17 ቀን 2018 ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ለመቅረብ የተለዩ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ 

 ዋና ዋና የጉባኤው አጀንዳዎችም የሀገር ግንባታ፤ የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት፤ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ጉዳይ፤ የሃይማኖት ጉዳዮች፤ የተቋማት ግንባታ፤ የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፤ ሙስናና መልካም አስተዳደር እና ሰላም ግንባታ ጉዳዮች ናቸው፡፡ 

በእነኚህ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይም ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ በሚጀምረው ጉባኤ ምክክር ይካሄድባቸዋል፡፡  

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ምክር ቤታቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመመስረት ረቂቅ አዋጅ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ቀደም ሲል በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ላይ ክፍተቶችን ጥለው ያለፉ የተናጥል ውሳኔዎችን ታሪክ ለመቀየር ትልቅ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገሪቱ ወቅታዊ ተግዳሮቶችና የተመረጡት አጀንዳዎች የተጣጣሙ መሆናቸውን አመልክተው፤ ምክክሩ ለቆዩ ችግሮች አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በዋናው ጉባኤ ላይ መላውን ማህበረሰብ የሚወክሉ ተሳታፊዎች ችግሮችን በትክክል በመለየትና በጋራ መፍትሔዎች ላይ በማተኮር ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በርካታ ችግሮቻቸውን በምክክር ከፈቱ ሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለ መግባባት ላይ ለመድረስ በጋራ መስራት እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡ 

ይህ አካሄድ እርስ በእርስ መግባባትን ከመፍጠር ባለፈ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ባህላችንን ለማሳደግ፣ ስልጡን ዜጋን ለመገንባትና ጠንካራ ሀገረ መንግስትን ለመመስረት ያስችላልም ብለዋል።

የእስካሁኑ የምክክር ሂደት ፍትሃዊና አካታች መሆኑን የገለጹት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት፣ በዋናው ጉባኤ የሚሳተፉ ተሳታፊዎች ከግል ፍላጎት ወጥተው ለአንድነትና ለሀገር ግንባታ ቅድሚያ መስጠት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡  

ጉባኤው ልዩነቶችን በማጥበብ ይበልጥ መቀራረብን የሚፈጥርና የጋራ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱበት ታላቅ መድረክ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

ይህ ታሪካዊ ምክክር ህዝቦች በጋራ በመከባበርና መተሳሰብ የሚኖሩባትን፣ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጥባት፣ በልማት ጎዳና የምትጓዝ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መሠረት እንደሚጥል ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም