ቀጥታ፡

የሸገር ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ 37 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል

ሸገር፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):- የሸገር ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ 37 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የከተማው የገቢዎች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የሸገር ከተማ አስተዳደር በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ ወረዳዎችንና ከተሞችን በማጣመር በቅርብ ዓመታት የተመሰረተ ሰፊና አዲስ ከተማ ነው። 

ከተማው ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ግዙፍ የኮሪደር ልማት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የከተማ ውበት ፕሮጀክቶችን በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። 

እነዚህን ሰፊ የልማት ፍላጎቶች በራስ አቅም ለመደገፍና የከተማውን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን የውስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግ ቀዳሚው የቤት ስራ ሆኖ ቆይቷል። 

ጽሕፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ የሰበሰበው ይህ ከፍተኛ ገቢ፥ የከተማዋን የልማት ፕሮጀክቶች በራስ አቅም ለመሸፈንና የህዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ ስኬት እንደሆነ ይታመናል።

የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ አምባው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 39 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር።

በበጀት ዓመቱም ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 37 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ስኬታማ የሆነው የታክስ አሰባሰብ ሥርዓትን ማሻሻልና ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱ እንዲሁም ለግብር ከፋዮች ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ መፍጠር በመቻሉ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ሕጋዊ ደረሰኝ የመቁረጥ ልምድን ማሳደግ፣ ቴክኖሎጂን በማስፋት ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ግልጽና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከፍሉ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው በዲጂታል መንገድ የሚጠበቅባቸውን ግብር እና ክፍያዎች መፈጸም መቻላቸውን ገልጸዋል።

ይህንን የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና ወደ ሙሉ ሥራ ለማስገባት ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።

የዘርፉን አዋጆችና መመሪያዎች በመከተል እንደ ታክስ ስወራ ያሉ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የተቀናጀ ኮሚቴ ተዋቅሮ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል በተሰሩ ሥራዎችም በበጀት ዓመቱ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ስድስት ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ሕጋዊ ደረሰኝ ባለመቁረጣቸው ምክንያት በ240 ነጋዴዎች ላይ የገንዘብና አስተዳደራዊ ቅጣት መጣሉን ገልጸው፤ በቀጣይም የዲጂታል አሠራርን በማዘመንና በደንበኞች ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም