ቀጥታ፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክር ቤት መግባታቸው በሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ በር ከፋች ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክር ቤት መግባታቸው በሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ በር ከፋች ነው ሲሉ ምሁራን ገለፁ።

ፓርቲዎቹ በብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መንግሥት ከሚመሰርተው ብልፅግና ፓርቲ ጋር ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ምሁራኑ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሰረት ብልፅግና ፓርቲ 438 አብላጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያገኘ ሲሆን በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፈዋል።

ውጤቱን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን እንደገለፁት፤ ምርጫው ኢትዮጵያ ወደተሻለ ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር ትልቅ መሰረት የጣለ ነው።

በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና አመራር ትምህርት ክፍል መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ኡጁሉ ኡኮክ እንደገለጹት፤ ከተለያዩ ፓርቲዎች የተውጣጣ ምክር ቤት መኖሩ የበሳል ዴሞክራሲ ግንባታ ምዕራፍን የሚያመላክት ነው።

በዚህም በምክር ቤቱ የበርካታ ፓርቲዎች ውክልና እንዲኖር በማድረግ የሀሳብ ብዝሃኃነት እንዲስተናገድ ዕድል እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።

ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ መንግሥት የሚመሰርተው ፓርቲና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይበልጥ ተቀራርበው በጋራ እንዲሠሩ በር ከፋች መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማታዊ ተግባቦትና የሚዲያ ጥናት መምህርና ተመራማሪ ዘለቀ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሕዝቡ ይወክሉኛል ያላቸው ፓርቲዎች ወደ ምክር ቤት መግባታቸው ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም በጋራ መሥራትን ያጠናክራል ብለዋል።

አዳዲስ ሕጎች ወይም አዋጆች ሲወጡ በምክር ቤቱ ውስጥ ጠንካራ ክርክርና የሀሳብ ፍጭት እንዲደረግባቸው ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።

ምሁራኑ አክለውም፤ በምርጫው አብላጫ ድምፅ ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ ሕዝቡ የሰጠውን ታላቅ አደራና ኃላፊነት በሚመጥን ቁመና ማገልገልና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ ወደ ምክር ቤት የገቡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን አደራ በመወጣት የተጀመሩ ሥራዎችን በማስቀጠል ሀገርን የማሻገር ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም