ቀጥታ፡

በዋናው የምክክር ጉባኤ ሙያዊ ማብራሪያ የሚሰጡ ባለሙያዎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጠር መስራት አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):- በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ወቅት ሙያዊ ማብራሪያ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች ውይይቱ በምክንያታዊነት የሚመራ እንዲሆን በእውቀት ላይ የተመሰረተ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጠር መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋናው ጉባኤ ወቅት ሙያዊ ማብራሪያ ከሚያቀርቡ ባለሙያዎች ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው። 


 

በመድረኩ ላይ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ፣ ሌሎች የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራን ታድመዋል።

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በጉባኤው ወቅት ሙያዊ ማብራሪያ የሚያቀርቡት ምሁራን ከተለያዩ የሙያ ዘርፎችና የሃላፊነት ደረጃዎች የመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ትልቅ ሀገራዊ ሃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ስራዎችን በስኬት ማከናወኑን አስታውሰዋል።

ዋናው የምክክር ጉባኤ ትልቅ የታሪክ ሂደት መሆኑንና ሂደቱም በስምንት የተለያዩ ቡድኖች ተከፍሎ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ምሁራኑ በጉባኤው ወቅት ለሙያቸው ብቻ ታማኝ በመሆን እውቀታቸውን ማካፈል እንዳለባቸውና ሂደቱ በምክንያታዊነት እንዲመራ የማስገንዘብ ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ በበኩላቸው፤ ለዋናው የምክክር ጉባኤ የሚሆኑ ስምንት አበይት አጀንዳዎች ተለይተው ይፋ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።


 

በዋናው ጉባኤ ላይ የሚሳተፉት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተመረጡ ተሳታፊዎች፣ የመላው ኢትዮጵያን ስብጥርና ብዝሃነት ባካተተ መልኩ በስምንት ቡድኖች ተከፋፍለው እንደሚዋቀሩ ገልጸዋል። 

ሙያዊ ማብራሪያ የሚያቀርቡት ባለሙያዎች፣ ውስብስብ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን ተሳታፊዎች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉበት መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ባለሙያዎቹ መሰረታዊ እውቀቶችን ለተሳታፊዎች በማስጨበጥ፣ በጉዳዮቹ ላይ የጋራና ግልጽ ግንዛቤ እንዲፈጠር የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባሳለፍነው ሰኔ 17 ቀን 2018 ለዋናው ሀገራዊ ምክክሩ ለመቅረብ የተለዩ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ 

ዋና ዋና የጉባኤው አጀንዳዎችም የሀገር ግንባታ፤ የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት፤ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬደዋ፤ የሃይማኖት ጉዳዮች፤ የተቋማት ግንባታ የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያያ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፤ ሙስናና መልካም አስተዳደር እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ናቸው፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም