የእርሻ ስራን በግብርና ባለሙያ በመታገዝ በማከናወናችን ምርታማነታችን አድጓል-የጉራጌ ዞን አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የእርሻ ስራን በግብርና ባለሙያ በመታገዝ በማከናወናችን ምርታማነታችን አድጓል-የጉራጌ ዞን አርሶ አደሮች
ወልቂጤ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):- የመኸር ወቅት የእርሻ ስራን በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ እያከናወኑ በመሆኑ ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን የጉራጌ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
የዞኑ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በግብርና ባለሙያዎች እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የተቀናጀ የግብርና ስነ-ዘዴን በመጠቀም በእንስሳት እርባታም ጭምር ውጤታማ ሆነዋል።
የእርሻ ስራን በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ እያከናወኑ በመሆኑ ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱንም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።
የአበሽጌ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ሰብስቤ ወልደሃዋርያት፤ አሁን ላይ ለዘር ምቹ ወቅት በመሆኑ በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው የግብርና ልማት ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም እስካሁን ሁለት ሄክታር መሬታቸውን በበቆሎ ዘር መሸፈናቸውንና አንድ ሄክታሩን ደግሞ በጤፍ ለመሸፈን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ የጌታ ወረዳ አርሶ አደር ጀማል ሟናጋ በበኩላቸው፤ ድንችን በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ተክለው በመንከባከባቸው ለምግብ ፍጆታ የሚውል ምርት ከማምረት ባለፈ ለገበያ ጭምር በማውጣት ትርፋማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ቀሪ አንድ ሄክታር ከግማሽ መሬታቸውን አርሰው በማለስለስ ሰብል ለመዝራት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
የሚደረግላቸው ሙያዊ ድጋፍ ምርታማነታቸውን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የተሳካ ስራ እንዲሰሩ ምክንያት እንደሆነ የገለፁት ደግሞ አርሶ አደር ገብሬ ዛጋ ናቸው።
የተቀናጀ የግብርና አሰራርን በመከተል የተለያዩ ሰብሎችን በማልማትና እንስሳትን በማርባት ተግባር ላይ መሰማራታቸው የተሻለ ኑሮ እንዲመሩ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ዘንድሮም ካላቸው የእርሻ መሬት ላይ አንድ ሄክታር መሬት በገብስ ለመሸፈን መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው ለዚህም የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ፤ በዞኑ በተያዘው መኸር ከ43 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
በመኸር እርሻ 180 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት መታረሱን ገልፀው እስካሁን 160 ሺህ የሚጠጋ ማሳ መልማቱን አስረድተዋል።
የግብርና ሜካናይዜሽንን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማላቅ እየተሰራ ያለው ስራ የዘርፉን ውጤታማነት እያሳደገው መሆኑንም አቶ አበራ አመልክተዋል።