ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን ከ 46 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የ2ኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጠ 

ደሴ ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ወሎ ዞን ከ46 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የ2ኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መስጠቱን የዞኑ መሬት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የገጠር መሬት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ምሳው አክቤ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ዘላቂ የመሬት ባለቤትነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ ናቸው።

ከዚህ ውስጥም በበጀት ዓመቱ ለ46 ሺህ 311 አርሶ አደሮች የ2ኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በመስጠት መሬታቸውን በዘላቂነት አልምተው እንዲጠቀሙ ተደርጓል ነው ያሉት።


 

የይዞታ ካርታው የአርሶ አደሩን ይዞታ በሳይንሳዊ መንገድ በመለካትና ማረጋገጫ በመስጠት የብድርና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት ሰፊ እድል የፈጠረ  እንደሆነም አስረድተዋል።

በተጨማሪም አርሶ አደሩ በይዞታው በሚያገኘው የብድር አገልግሎት  የግብርና ስራውን ለማዘመን የሚያስችለው ከመሆኑ  ባለፈ ሌሎች የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ እንዲሰማራ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ብቻ አራት ሺህ 693 አርሶ አደሮች ከ127 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን  አስረድተዋል።

በዞኑ ደሴ ዙሪያ ወረዳ የ032 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ ሰይድ ፣የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘቴ መሬቱን በተሻለ መንገድ ለማልማትና ተጨማሪ ሀብት ለማፍራት አስችሎኛል ብለዋል።

ቀደም ሲል የነበረው ይዞታ ትክክለኛ ልኬት ያልነበረው በመሆኑ ከሌላ ባለመብት ጋር የመገፋፋት ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር አስታውሰው ፣ አሁን ችግሩ ሙሉ ለሙሉ መፈታቱን ገልጸዋል።

"የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታው ወሰንና ልኬትን በትክክል ያስቀመጠ በመሆኑ የመሬታችንን ዘላቂ ዋስትና ያረጋገጠ ነው" ያሉት ደግሞ የወረኢሉ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጀማል ዋሴ ናቸው።

ይህም ይገባኛል በሚል ይፈጠሩ የነበሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በማስቀረቱ ምርታማነታችን ለመጨመር ያግዘናል ነው ያሉት።

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የ2ኛ ደረጃ የመሬት ማረጋገጫ ካርታ መስጠት መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም