የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፈረንሳይ ሊዮን የበረራ አገልግሎት አፍሪካን ከዓለም ለማገናኘት በሚደረገው ጉዞ ቁልፍ ምዕራፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፈረንሳይ ሊዮን የበረራ አገልግሎት አፍሪካን ከዓለም ለማገናኘት በሚደረገው ጉዞ ቁልፍ ምዕራፍ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/ 2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፈረንሳይ ሊዮን የበረራ አገልግሎት አፍሪካን ከዓለም ለማገናኘት በሚደረገው ጉዞ በቁልፍ ምዕራፍነት እንደሚወሰድ የአየር መንገድ ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፈረንሳይ ሊዮን አዲስ የመንገደኞች በረራ አገልግሎትን አስጀምሯል።
የአየር መንገድ ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፤ የፈረንሳይ የኢኮኖሚ፣ የባህልና የፈጠራ ብልፅግና ማዕከሏ ሊዮን የሚደረገው በረራ የተደራሽነት አድማስን ያሰፋል ብለዋል።
ወደ ሊዮን ከተማ የሚደርገው በረራም የአውሮፓ መዳረሻውን ወደ 23ኛ በማሳደግ የፈረንሳይ ከተሞች ከአፍሪካ ጋር በማገናኘት ስኬታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንድ በፈረንሳይና የአውሮፓ ከተሞች የሚያደርገው የበረራ አገልግሎትም የኢትዮ-አውሮፓን ግንኙነት በማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ለደንበኞቹ በሚያቀርባቸው ጥራትና ብቃት ያላቸው የበረራ አገልግሎቶችም ዓለም አቀፍ የአቭዬሽን ኢንዱስትሪ ስመጥሩነቱን በተግባር እያስመሰከረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በሚቀጥለው በጀት ዓመትም አምስት አዳዲስ የበረራ አገልግሎትን በማስጀመር ኢትዮጵያና አፍሪካን በዓለም የንግድ፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የማስተሳሰር ሚናውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
አየር መንገዱ የበረራ አገልግሎት ጥራትን ለማላቅም ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በላቀ ቴክኖሎጂዎችና በደንበኛ ተኮር አገልግሎት ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ወደ ፈረንሳይ ሊዮን ለሚደረገው የበረራ አገልግሎት መሳካት ድጋፍና ትብብር ላደረጉ ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ወደ ፈረንሳይ ሊዮን ያስጀመረው የበረራ አገልግሎት የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በተለይም የኢትዮ-ፈረንሳይን ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት በህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር እንደሚረዳ አስረድተዋል።