መቀሌ 70 እንደርታ እና ድሬዳዋ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
መቀሌ 70 እንደርታ እና ድሬዳዋ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/ 2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ38ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች እየተደረጉ ይገኛል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ መቀሌ 70 እንደርታ ነገሌ አርሲን 3 ለ 0 አሸንፏል።
መሃሪ አምሃ፣ ብርሃኑ አዳሙ (ፍጹም ቅጣት ምት) እና ፍሬዘር ካሳ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ከሊጉ የወረደው መቀሌ 70 እንደርታ በውድድር ዓመቱ ስምንተኛ ድሉን በማስመዝገብ በ40 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በአንጻሩ በሊጉ ስምንተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ነገሌ አርሲ በ60 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሷል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።
አስራት ቱንጆ እና አብዲሳ ከማል የማሸነፊያ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፏል። መሪሁን መስቀለ ለአርባምንጭ ከተማ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል።
በሊጉ ዘጠነኛ ድሉን ያስመዘገበው ድሬዳዋ ከተማ በ42 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል።
የ21 ዓመታት ረጅም የኳስ ዘመኑን አጠናቆ ከትናንት በስቲያ የመሰናበት ውሳኔውን ያሳወቀው አንጋፋው የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች መስዑድ መሐመድ፣ የመጨረሻ ጨዋታውን አድርጎ በክብር ተሸኝቷል።
አርባምንጭ ከተማ በውድድር ዓመቱ የገጠመውን 17ኛ ሽንፈት ተከትሎ፣ በ35 ነጥብ በሊጉ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ተገዷል።
ድሬዳዋ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸው ይታወቃል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ መድን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።