ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የአገልግሎት ጥራትን በማስጠበቅ እመርታዊ ለውጥ እያመጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/ 2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የአገልግሎት ጥራትን በማስጠበቅ እመርታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ አስታወቁ።

ሚኒስትር ዴኤታው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አጠቃላይ የፍትሕ ስርዓትን ለማሻሻል በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በክልል ፍትሕ ቢሮዎችና ባለድርሻ አካላት ቅንጅት በርካታ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ሀገር አቀፍ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱንና በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል። 

በየክልሉ የሚገኙ ባህላዊ የማህበረሰብ ፍትሕ ሥርዓቶች ጉዳዮችን መርምረው ውሳኔ እንዲሰጡና ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ በሁሉም ክልሎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡን የሚያማርሩ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና በተቋማት ያሉ የአሠራር ሥርዓቶችን የሕግ ቅርጽ ለማስያዝ እና በአግባቡ አገልግሎት የማይሰጡ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልፀዋል።

በወንጀል ምርመራ ስራ የፌዴራልና ክልል ፍትሕ ተቋማት በጋራ በመቀናጀት በርካታ ስራዎችን ማከናወናቸውን አንስተው በፌዴራል ደረጃ ወጥተው በክልል መውጣት የሚገባቸው ህጎች እንዲወጡ የክትትልና ድጋፍ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የአስተዳደር ፍትሕን በማስፈን ረገድ ደግሞ አብዛኛዎቹ ክልሎች የአስተዳደር አካሉን የሚቆጣጠርና በየተቋማቱ የሚሰጡ ውሳኔዎችን የሚከታተል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ማጽደቃቸውን ገልጸዋል። 

ይህ አዋጅ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ የሚሰጡ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።

በጥራትና በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ መሠረታዊ ሕጎች እንዲወጡና የሕግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁ ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አስታውሰዋል።

በቅርቡ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች በጋራ የሚመሩበት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

በ2019 በጀት ዓመት አዳዲስና ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን ግልጽ ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

በፍትሕ ዘርፉ የተጀመረው ሀገራዊ ሪፎርም ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲወጡም ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም