ቀጥታ፡

በዞኑ በበጋ መስኖ ልማት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል

ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 24/ 2018 (ኢዜአ):- በምስራቅ ጎጃም ዞን የበጋ መስኖ ልማት ስራን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ  መቻሉን የዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ካሳሁን ዘለቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤የበጋ መስኖ ልማት ስራ አርሶ አደሩ የዝናብ ወቅትን ጠብቆ ከማምረት እንዲወጣ በማድረግ ለውጥ ለማስመዝገብ አስችሏል።

አርሶ አደሩ በበጋ መስኖ ልማት ስራ በስፋት እንዲሰማራ የተከናወነውን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ጨምሮ በወቅቱ ግብአት እንዲቀርብለት መደረጉም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ያስቻለ መሆኑን አንስተዋል።

ለአብነትም በዘንድሮው በጋ ወራት ከ 50 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬትን በመስኖ በማልማት ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ  ምርት መገኘቱን ጠቁመዋል።

የመስኖ ልማቱ ይበልጥ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲያስችልም ከ67 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን አስረድተዋል።

በመስኖ ልማት ስራው 100 ሺህ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን የተገኘው ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር  ሲነፃፀር  ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ አለው ብለዋል።

ለተገኘው ስኬት የግብርና ቴክኖሎጂ  አጠቃቀምን ጨምሮ የባለሙያዎች የተጠናከረ ድጋፍ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

በበጋው ወራት መስኖ ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል  የማቻከል ወረዳ የየውላ ቀበሌ  አርሶ አደር አዲሱ ይዘንጋው ፤ ባላቸው አንድ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ እና በቆሎ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የመስኖ ልማት ስራው ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት እና በሁለት ዙር በማምረት ከቤት ፍጆታ አልፎ ለገበያ  የሚቀርብ ምርት እንዲያገኙ በማድረግ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።

ከባለሙያዎች ያገኙትን ግንዛቤና ግብአት በመጠቀም  በመስኖ ልማት ስራ በመሰማራት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የጓያና የጓሮ አትክልትን አልምተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ በዞኑ የአነደድ ወረዳ የወጀል ቀበሌ  አርሶ አደር እንዳላማው ጫኔ ናቸው።

የበጋ መስኖ ስራ የተለያዩ ሰብሎችን በማልማትና በማስፋፋት ኑሮዋቸውን ለመቀየር እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም