በወላይታ ዞን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ወላይታ ሶዶ ፤ ሰኔ 24/2018(ኢዜአ)፦ በወላይታ ዞን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አሰባሰብ ሂደትን በመጠቀም ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።
የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ከዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ጋር በመተባበር የ2018 ዓ/ም የግብር ዘመን የታክስ አሰባሰብና የ2019 የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ንቅናቄ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
በመድረኩ የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ ታደሰ በዘንድሮ በጀት ዓመት 5 ነጥብ 51 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከ ሰኔ 23/2018 ዓ.ም ድረስ 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ይህም አፈፃፀሙን 95 በመቶ ማድረሱን አንስተው ተግባሩ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የገቢ አሰባሰቡ ዲጂታል የተደገፈው አሰራርና የባለሙያዎች ቁርጠኝነት የተሻለ ገቢ እንዲሰበሰብ ማገዙን አስረድተዋል።
ከመረጃ አያያዝና ትንተና ጀምሮ በገቢ አሰባሰብ ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በጋራ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ከሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ የግብር ዘመኑ የታክስ አሰባሰብና የንግድ ፈቃድ ዕድሳት እንደሚጀመርም ገልጸዋል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ታዴዎስ በበኩላቸው ዞኑ በተለያዩ ዘርፎች የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ውጤቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ተቀናጅተው በመስራታቸው የመጣ መሆኑን በማንሳት ቀጣይ የህዝቡን አዳጊ የልማት ፍላጎት ለማሟላት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የዞኑ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ እንቅፋት የሆኑ እንደ ህገወጥ ንግድና ያለደረሰኝ የሚደረገውን ግብይት በቁርጠኝነት መቆጣጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።
የንቅናቄ መድረኩ ዓላማም የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እና የንግድ ስራ ፈቃድ ዕድሳት ተግባርን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ምክክር ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል።
በመድረኩም የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።