ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቶች በዩጋንዳ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ ቀረበላቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/ 2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ አትሌቶች እና የሩጫ አፍቃሪያን በዩጋንዳ ካሲሴ ከተማ በሚካሄደው አምስተኛው የሩዌንዞሪ ማራቶን ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ጥሪውን ያቀረቡት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከተስከር ላይት ሩዌንዞሪ ማራቶን ጋር በመተባበር ነው።


ይህ ጥሪ በኢትዮጵያና ዩጋንዳ ሀመካከል ያለውን የሩጫ ባህልና ማህበረሰባዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በኡጋንዳ ካሴሴ ከተማ ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚካሄደው ይህ ውድድር የዓለም አትሌቲክስ እውቅና የተሰጠው የጎዳና ላይ ሩጫ ነው።

የሩዌንዞሪ ማራቶን በአደረጃጀቱና በአትሌቶች ጥራት በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ 200 ውድድሮች አንዱ ለመሆን መብቃቱ በመረጃው ላይ ተመላክቷል።

ውድድሩ ከማራቶን ባለፈ፣ የአምስት ኪሎ ሜትር፣ 10 ኪሎ ሜትር እና 21 ኪሎ ሜትር ግማሽ ማራቶን ይስተናገዱበታል።

ከኢትዮጵያ የሚሄዱ ሯጮች በኢትዮጵያ የክረምት ወቅት የሚኖረውን ቅዝቃዜና ዝናብ በመቀየር፣ በምድብ ወገብ (ኢኩዌተር) መስመር ላይ በሚገኘው የካሴሴ ሞቅ ያለ ፀሐይና ሞቃታማ የሳር ምድር (ሳቫና) ውስጥ የመሮጥ ልዩ ዕድል ያገኛሉ።

ውድድሩ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅር (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ በሆነው የንግስት ኤልሳቤጥ ብሔራዊ ፓርክ የሚጀምር ሲሆን፣ በከበሮና በሙዚቃ በምትደምቀው የካሴሴ ከተማ መንገዶች አድርጎ፣ በበረዶ በተሸፈኑት የሩዌንዞሪ ተራሮች ግርጌ በሚገኘው አስደናቂው የኪሌምቤ ሸለቆ ድረስ ይዘልቃል።

ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ በተካሄደው ሲቢኢ ሩጫ ላይ የተሳተፉ እና ሌሎችም የሩጫ አፍቃሪያን በሩዌንዞሪ ማራቶል ለመሳተፍ መመዝገብ እንደሚችሉ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቋል።

የሩዌንዞሪ ማራቶን ከእ.አ.አ 2022 አንስቶ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም