የአገልግሎት እመርታ በመሶብ - የዜጎች እፎይታ እና የተሳለጠ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የአገልግሎት እመርታ በመሶብ - የዜጎች እፎይታ እና የተሳለጠ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2018 (ኢዜአ)፡-የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን እንግልት በመቀነስ ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ማስቻሉን ተገልጋዮች ገለጹ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የዜጎችን እንግልት በመቀነስና የመንግሥት አሰራርን በማዘመን ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው።
ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አሰራርን በአንድ ቦታ ላይ በማቅረብ፣ ዜጎች የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች ያለምንም ውጣ ውረድ ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ምቹ በሆነ ሁኔታ እንዲያገኙ አድርጓል።
ይህም የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ከማሳለጡ ባለፈ፣ አጠቃላይ አሰራሩን ግልጽ በማድረግ ብልሹ አሰራርን በከፍተኛ ሁኔታ መከላከል ችሏል፡፡
የማዕከሉን አገልግሎት በተመለከተ ለኢዜአ አስተያየት የሰጡት የመዲናዋ ነዋሪ አቶ ደስታ ወዳጄነህ፣ የዲጂታል መሶብ አገልግሎት መዘርጋቱ ውድ ጊዜን የሚቆጥብና ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የአገልግሎት ምዕራፍ እየገባች መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
አሰራሩ ዜጎች በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም እንደረዳቸውና ቀደም ሲል ትልቅ ፈተና የነበረውን እንግልት ያስቀረ አሠራር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛው ነዋሪ አቶ ዮሴፍ ታመነ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል መታወቂያ ለማውጣት ብዙ መመላለስና አድካሚ ውጣ ውረዶች የነበሩ መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን ግን በአዲሱ አሰራር ፈጣን አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ረጅም ጊዜ ይወስድ የነበረው አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እንዲጠናቀቅ መደረጉ ነዋሪዎች በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡና በቅልጥፍና እንዲስተናገዱ እንዳገዛቸው ጠቁመዋል፡፡
ይህም በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችንና ተያያዥ ቅሬታዎችን ሙሉ በሙሉ ያስቀረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ይርጋለም ተሾመ በበኩላቸው፣ የዲጂታል መሶብ አገልግሎት አሰጣጥ እጅግ የተራቀቀና ቅልጥፍና የተሞላበት በመሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ መነሻ የሚሆን ነው ብለዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር በአጠቃላይ በሀገሪቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠውና ለቀጣዩ ትውልድ መልካም አሻራ የሚጥል መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አስቻለው አድማሱ፣ የመሶብ አገልግሎት ቀደም ሲል በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ በርካታና ውስብስብ ችግሮችን ያስወገደ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ዘመናዊ የዲጂታል አሰራር በግለሰብ ደረጃ ምቾትን ከመፍጠሩ ባለፈ፣ እንደ ሀገርም ትልቅ እድገትና እምርታ መሆኑን በተጨባጭ ማረጋገጡን አስረድተዋል።
አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል መሰጠታቸው አላስፈላጊ መጉላላቶችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ነዋሪ አቶ ብርሃን አብርሃ ናቸው።
አቶ ብርሃን ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር እጅግ አድካሚና ውጣ ውረድ የበዛበት እንደነበር አስታውሰው፣ የአሁኑ ግን የተቀላጠፈና ምቹ መሆኑን መስክረዋል።