የምክክር ኮሚሽኑ የለያቸው አጀንዳዎች ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ ያስችላሉ -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ኮሚሽኑ የለያቸው አጀንዳዎች ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ ያስችላሉ -ምሁራን
ጅማ፤ ሰኔ 24/2018 (ኢዜአ)፦ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የለያቸው አጀንዳዎች ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ ያስችላሉ ሲሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሚቀርቡ አጀንዳዎች መካከል የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም የፌደራል ከተሞች ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ ታሪካዊ ቅሬታዎች እና እርቅን የሚመለከቱ ጉዳዮች፣ ተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነትና ሰብአዊ መብቶች፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስና እና መልካም አስተዳደር እና ሰላም ግንባታ ምክክር የሚደረግባቸው አንኳር ጉዳዮች ናቸው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ለሀገር ግንባታ በስልጡን የፖለቲካ አካሄድ መመካከር መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ምሁራን ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንም የጀመረው ተግባር ይህን ለማሳካት ድርሻው የጎላ መሆኑን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናግረዋል።
ምክክር በሃሳብ የበላይነት ለሀገር የሚበጅ አማራጭ ፖሊሲ የሚነደፍበት በመሆኑ፣ ለተግባራዊነቱም የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።
ሀሳባቸውን ከሰጡት መካከል በዩኒቨርሲቲው የሕዝብ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ፍቃዱ ቶለሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ብዙኃንን ያሳተፈ ምክክር ከቅቡልነቱም በላይ ዘላቂ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ አጋዥ ነው።
በዚህ ረገድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሕዝቡን በየደረጃው በማሳተፍ የለያቸው አጀንዳዎች፣ የቆዩ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሂደቱም ሕዝብና ሲቪል ማህበራት የነበራቸው የነቃ ተሳትፎ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ጉዳይ በጋራ መስራት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግም ሀገራዊ ነባር ባህልን መተግበር እንደሚገባ መክረዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል መሐመድ በበኩላቸው፤ ሀገር በቀል የውይይትና የምክክር እሴቶችን ወደ ፖለቲካ ባህል ማምጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ችግሮችን በምክክር የመፍታት ሂደት ሥራ ላይ መዋሉ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማሳካት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን ሥራም ጉዳዮችን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት የሄደበት ርቀት የሚበረታታና አዲስ የፖለቲካ ባህል ለማስረጽ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።