ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት መርሐ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/ 2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 38ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት መቀሌ 70 እንደርታ ከነገሌ አርሲ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

መቀሌ 70 እንደርታ በ37 ነጥብ 19ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ከሊጉ መውረዱ ይታወቃል።

ነገሌ አርሲ በ60 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ጨዋታው ለወራጁ መቀሌ 70 እንደርታ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ላረጋገጠው ነገሌ አርሲ የውድድር ዓመቱን በድል ለመቋጨት ይጫወታሉ።

በሌላኛው መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ድሬዳዋ ከተማ በ39 ነጥብ 18ኛ አርባምንጭ ከተማ በ35 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዘዋል። ሁለቱም ቡድኖች ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸው ተረጋግጧል።

ጨዋታው ለቡድኖቹ ከመርሐ ግብር ማሟያነት የዘለለ ትርጉም የለውም።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ መድን በአዳማ ሳይንንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ፋሲል ከነማ በ52 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በ46 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።

በ37ኛው ሳምንት ፋሲል ከነማ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1 ለ 0 ሽንፈት ሲያስተናግድ ኢትዮጵያ መድን በምድረ ገነት ሽሬ 3 ለ 0 ተረቷል።

ሁለቱም ቡድኖች ዓመቱን በድል ለማጠናቀቅ ይፋለማሉ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 38ኛ ሳምንት እስከ ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

አቤል ያለው (ሲዳማ ቡና)፣ ታምራት እያሱ (ፋሲል ከነማ) እና ናትናኤል ዳንኤል (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) በተመሳሳይ 14 ግቦች የሊጉን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃ በጋራ እየመሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም