ኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ አቅጣጫን ተግባራዊ በማድረጓ በሁሉም መስክ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ አቅጣጫን ተግባራዊ በማድረጓ በሁሉም መስክ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ አቅጣጫን ተግባራዊ በማድረጓ በሁሉም መስክ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ከግብርና መር የኢኮኖሚ አቅጣጫ ወደ ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መሸጋገሯ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መከተል ከጀመረች ወዲህ በሁሉም ዘርፎች የሚያስደንቅ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በግብርና ዘርፍ በስንዴ፣ በቡና፣ በሩዝ፣ በፍራፍሬ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በዶሮና ወተት የተገኙ ውጤቶች አስደናቂ ናቸው ብለዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ዘርፍም በ5 ሚሊዮን ኮደርስ፣ በዲጂታል መታወቂያ፣ በሞባይል መኒ፣ በቴሌ ብር አንጸባራቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ዘርፍም ለዘመናት ውስን አቅም የነበረው ዘርፍ እንደነበር አውስተው፤ አሁን ላይ ግን እጅግ በተሻለ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ከዘርፉ የሚገኙ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ማስገባት ሳይችል የቆየው የማዕድን ዘርፍ አሁን ላይ ቢሊዮን ዶላር የሚገኝበት ዘርፍ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዚህ ዓመት ከአጠቃላይ ወጪ ንግድ ከ10 ነጥብ 78 እስከ 11 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ ተግባራዊ በመደረጉ ሁሉም ዘርፍ የራሱን ድርሻ እንዲያዋጣ እና ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ አድርጓል ነው ያሉት።
በመሆኑም በዚህ ዓመት 10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
ዓመታዊ ገቢ የመሰብሰብ አቅም እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር እንደምትሰበስብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ አቅጣጫን ተግባራዊ በማድረጓ በሁሉም መስክ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን ነው የተናገሩት፡፡
ይህም የመንግስትን ትክክለኛ እና የተሳሰረ የፖሊሲ ተግባራዊ ውጤት ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡