ቀጥታ፡

የቱሪዝም መሰረተ ልማት ግንባታ የሀገሪቱን ስነ ምህዳርና ዘላቂ ልማትን ባገናዘበ መልኩ እየተከናወነ ነው -  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፡-የቱሪዝም መሰረተ ልማት ግንባታ የሀገሪቱን ስነ ምህዳርና ዘላቂ ልማት ባገናዘበ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ቱሪዝም-አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር" በሚል ከኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የቱሪዝም መሰረተ ልማት ስነ-ምህዳርን፣ ዘላቂ ቱሪዝምን እና አረንጓዴ ልማትን ባካተተ መልኩ እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

የቱሪዝም ዘርፍ ማነቆዎችን ለመፍታት መሰረተ ልማት በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፍሎ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል፡፡ 

በዚህም የመዳረሻ ስፍራዎች ልማት፣ የቱሪስቶች ማረፊያ ቦታዎች፣ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት እንዲሁም የዲጂታል መሠረተ ልማቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ሰባት ተጨማሪ ኤርፖርቶች ተመርቀው ስራ የጀመሩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹም በቅርቡ ስራ ይጀምራሉ ብለዋል። 

ባለፉት ስድስትና ሰባት ዓመታት የተከናወኑት የገበታ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳረፍ መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በገበታ ለሀገርና ለትውልድ የአርባምንጭ እና የጅማ ፕሮጀክቶች ከሞላ ጎደል ያለቁ ሲሆን፤ የአርባ ምንጭ ፕሮጀክት በቅርቡ ይመረቃል ብለዋል።

የኮሪደር ልማትና የሪዞርቶች ተፅዕኖን ሲገልጹም በአርባ ምንጭ፣ በጎርጎራ፣ በሀይቅ፣ በጅማ እና በጅጅጋ (ሸበሌ) የተገነቡት ሪዞርቶችና የኮሪደር ልማቶች የአካባቢውን ከተሞች ገጽታ በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ተጨባጭ ተፅዕኖ እያመጡ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡ 

የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት የተጠቀሟቸው የኢንቨስትመንት ምንጮች እጅግ የተለያዩ ሲሆኑ በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እነኚህም የመንግስትና የግል አጋርነት፣ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲሁም የወዳጅ ሀገራት ድጋፍ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ እየታየ ያለው የቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት የዜጎች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የውጭ ወዳጅ ሀገራት እና የግለሰቦች የሀብት፣ የሀሳብና የእውቀት ድምር ውጤት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

 

 
 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም