ቀጥታ፡

የታሪካዊ ቅርሶች ዕድሳት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግና የሀገርን ገጽታ ለመቀየር ያለመ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች እያከናወናቸው ያሉ የቤተ-መንግሥታት ዕድሳትና የቱሪስት መዳረሻዎች የማልማት ተግባራት ቅርሶችን ከመጠበቅ ባለፈ፣ የቱሪዝም ዘርፉን የኢኮኖሚ ሞተር ለማድረግ ያለሙ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ከኤን.ቢ.ሲ ኢትዮጵያ ጋር "አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር" በሚል ርዕስ በቱሪዝም ዘርፍ ዙሪያ ባደረጉት ልዩ ቆይታ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የተከናወኑ የቱሪዝም ልማት ፍሬዎች መንግሥት ቅርሶችን ጠባቂ፣ አሻጋሪና አዳሽ እንጂ አፍራሽ አለመሆኑን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከ35 በላይ በተለያዩ ዘመናት ከኢትዮጵያ የተወሰዱና የተዘረፉ ቅርሶችን ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

ቅርሶችን የምናስመልስና የምንጠብቅ እንጂ የምናፈርስ አይደለንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች ላይ የተከናወኑት የዕድሳት ሥራዎች የቅርሶቹን ይዘትና ደህንነት በከፍተኛ ጥንቃቄ የጠበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለአብነትም የጎንደር ፋሲለደስ ግንብ ለመቶ ዓመታት ያህል ሳይታደስ በቁሙ እየፈረሰና ግቢውም አሳዛኝ ሁኔታ ላይ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የተከናወነው ዘመናዊና ጥንቃቄ የተሞላበት ዕድሳት ለሚቀጥሉት 50 እና 60 ዓመታት ለትውልድ የሚሻገር እና ማንኛውም ጎብኝ የሚኮራበት መሆኑን ገልጸዋል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዕድሳት በውጭ ሀገር ባለሙያዎች አማካኝነት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ቀደም ሲል በመሠረተ-ልማት እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች ለመግባት አስቸጋሪ የነበረው የሶፍ ኡመር ዋሻ አሁን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ተደርጎበት ለጎብኝዎች ምቹ መደረጉን ጠቁመዋል።

የጀጎል ግንብም ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ውብ ሆኖ መታደሱን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ቀደም ሲል ግቢው ያረጁ ተሽከርካሪዎችና መሣሪያዎች የተሰበሰቡበት እንዲሁም የመሬት ውስጥ ክፍሉ በጎርፍ የተሞላና ለአያያዝ አስፈሪ የነበረ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ የሚጎበኘውና የሚኮራበት ስፍራ ሆኗል ብለዋል።

የቤተ መንግሥት ተሽከርካሪዎችን አድሶ ሥራ ላይ ማዋል ከፍተኛ ጥረት መጠየቁን አንስተው፤ ይሄንን እውነታ ወደ ጎን በመተው ቅርስ ተበላሸ የሚሉ ሀሳቦች በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሠረቱ ናቸው ብለዋል።

መንግሥት በቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ላይ የተከተለው መርህ ጥራትን እና ትክክለኛነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሀገሪቷ የሚገነቡትና የሚታደሱት መዳረሻዎች ሁሉንም ሃይማኖቶች፣ ሁሉንም አካባቢዎችና ታሪኮች በእኩልነት የሚያንጸባርቁና የኢትዮጵያን አጠቃላይ መልክ በአንድነት የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ባለሙያዎች የሚከናወኑት የልማት ሥራዎች በከፍተኛ የአመራር ክትትልና ትኩረት የሚመሩ በመሆናቸው የዕድሳትና ግንባታ ሂደታቸው ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑት ሥራዎች ኢትዮጵያ ለዓለምና ለዜጎቿ የምታሳያቸውን ድንቅ ሀብቶች የገለጡ መሆናቸውን በማንሳት የተመዘገበው ውጤት እጅግ የሚያስደስት መሆኑን አመልክተው፤ መንግሥት የቅርሶች “አስዋቢና ዓይን ገላጭ” መሆኑን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም