የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን ነው -የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን ነው -የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን ነው ሲሉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ያሳተፈው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢሚስበርገር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው።
የአውሮፓ ኅብረት በፀሐይና በንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በመስኩ ዴንማርክ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረገች መሆኗን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ ፈረንሳይም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመሆን መሰል ኢንቨስትመንቶችን በኢትዮጵያ ለማካሄድ ግብ መያዙንም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ተግዳሮቶች ሁሉንም ሀገራት የሚነኩ መሆናቸውን ገልጸው፤ የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና አካባቢ ጥበቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ መሪ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የተቀናጀና የተደራጀ አካሄድ መከተሏ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሮማንያ አምባሳደር ዩሊያ ፓታኪ ዛሬ በእንጦጦ ፓርክ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፌ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የተገኘው ውጤት ሌሎች ሀገራትንም የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገራት ይሄንን ልምድ ሞዴል አድርገው ሊተገብሩት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ የኦማን ኤምባሲ ሚሽን ኃላፊ አፍካር አል ፋርሲ በበኩላቸው፤ የኦማን መንግሥት በአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።