ኢትዮጵያን ወደ ዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያ ለማስገባት የሕግ ማዕቀፎችን በመቅረጽ ረገድ መሠረታዊ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ወደ ዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያ ለማስገባት የሕግ ማዕቀፎችን በመቅረጽ ረገድ መሠረታዊ ተግባራት ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ወደ ዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያ ለማስገባት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ረገድ መሠረታዊ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን ገለጹ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲቱዩትና በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ትብብር "የካርቦን ገበያዎች፣ በኢትዮጵያ እድሎች፣ አስተዳደርና ለዘላቂ ግብርና ልማት እንድምታ" በሚል መሪ ሃሳብ አውደ ጥናት ተካሒዷል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስዩም መኮንን የካርቦን ግብይት ሙቀት አማቂ ጋዝን ለመቀነስ የተዘረጋና ጋዝን የመከቱ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት ዓለም አቀፍ ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራ፣ በታዳሽ ኃይልና በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፎች በርካታ አበረታች እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2050 የጋዝ ልቀትን ወደ ዜሮ ለማድረስ በስትራቴጂ የተደገፈ ግብ አስቀምጣ እየሰራች የምትገኝ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅና ማስገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
ይህንኑ ስኬት እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ለመጠቀምም ባለፉት ጊዜያት አዋጅ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ወደ ገበያው ለመግባት የሚያስችሉ መሠረታዊ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ የአየር ንብረት ለውጥ የወቅቱ የዓለማችን አሳሳቢ ስጋት መሆኑንና ድርቅ፣ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በካርቦን ገበያ ላይ በስኬት ለመሳተፍ የሚያስፈልጉ በርካታ መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታዎችን አስቀድማ ማዘጋጀቷንም ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የመደመር መንግሥት ለአካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሰጠው ልዩ ትኩረት የሀገሪቱን ዝግጁነት ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር ከካርቦን ገበያ የሚገኘውን ሀገራዊ ገቢ ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ለካርቦን ገበያው ስኬታማነትና ለዘላቂ ግብርና ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በተለይም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉና የደን ልማትን የሚያፋጥኑ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።