የኢጋድ የሳይበር የተግባር ልምምድ የአባል ሀገራትን የጋራ ደህንነት ለማረጋገጥና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ የሳይበር የተግባር ልምምድ የአባል ሀገራትን የጋራ ደህንነት ለማረጋገጥና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የኢጋድ የሳይበር የተግባር ልምምድ የአባል ሀገራትን የጋራ ደህንነት ለማረጋገጥና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የስልጠናው ተሳታፊ ሀገራት ተወካዮች ገለጹ።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሣ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢጋድ ቀጣናዊ የሳይበር የተግባር ልምምድ ሥልጠና ላለፋት አምስት ቀናት በአዲስ አበባ ተሰጥቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና የጅቡቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በጅቡቲ የሚገኘው የኢጋድ ዋና መሥሪያ ቤት የሳይበር ደህንነት እና የዳታ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሙያ ኸድራ አሊ ዩሱፍ እንደገለጹት፤ ሥልጠናው ከፖሊሲ ቀረጻ ጀምሮ እስከ ቴክኒካዊ ልምምድ ድረስ ያሉ በርካታ ዘርፎችን ያካተተ ነበር ብለዋል።
በተለይም የሳይበር ደህንነት ሥጋት መረጃ ትንተና እና የማልዌር ወይም የጎጂ ሶፍትዌሮች ምርመራ ላይ ሰፊ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል።
የሳይበር ሥጋቶችና ጥቃቶች በተፈጥሮ ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው መርሃ ግብሩ በአባል አገራቱ መካከል ያለውን የጋራ የመከላከል አቅም እና ቀጣናዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በኡጋንዳ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ውስጥ ዋና የሲስተምስ አድሚኒስትሬተር ሮበርት ልዋሳ እንደተናገሩት፤ መርሃ ግብሩ እንደ ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ያሉ የኢጋድ አባል አገራት የሳይበር ደኅንነትን እንዴት እየተገበሩት እንደሆነና ያላቸውን የአስተዳደር መዋቅር እርስ በእርስ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
የሳይበር ጥቃት ድንበር ተሻጋሪና ዓለም አቀፋዊ ሥጋት መሆኑን በመጥቀስ ጥቃቶቹን ለመቋቋም ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታና አብሮ መስራት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በደቡብ ሱዳን የብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ቁጥጥር ማዕከል አናሊስት ዮም ማሉአል ማጆክ በበኩላቸው፤ ሥልጠናው ሙሉ በሙሉ በተግባር እና በእውነተኛው ዓለም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን መነሻ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በየአገራቱ የሚገኙ የመንግሥት መሠረተ ልማቶችን፣ የፋይናንስ ሥርዓቶችን እና የግል ተቋማትን ከጥቃት ለመጠበቅ የትኞቹ ሰርቨሮችና ሥርዓቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ትልቅ ግንዛቤ ያገኘንበት ነው ብላለች።
ወደ አገራቸው ሲመለሱም ይህንን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
የሶማሊያ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኮምፒውተርና መረጃ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን መሐመድ በበኩላቸው ሥልጠናው እጅግ አስደናቂና ከፍተኛ እውቀት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ በሳይበር ደኅንነት ዘርፍ ያላትን ልምድና ያሳየችውን ዕድገት ማጋራቷ ለአባል አገራቱ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎችም ሰፊ እውቀትና ልምድ ማግኘታቸውን በመግለጽ ተሳታፊዎቹ በሥልጠናው መደሰታቸውን አክለዋል።