ቀጥታ፡

የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ጥገናን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው

ኮምቦልቻ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፡- የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥገናን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን  የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ ። 

የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በቅርቡ የጥገና ስራ የተጀመረውን የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክትን ዛሬ ጎብኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ህሊና በላቸው እንደገለፁት፣ ባቡር መስመሩ የወጭና ገቢ ንግድን በማሳለጥ ለአገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረውን የባቡር መስመር የጥገና ስራን  በጥራትና በፍጥነት ገንብቶ ለአገልግሎት ለማብቃት በተለየ ቅንጅት እየተሰራ መሆኑንገልጸዋል።

በዛሬው እለትም የኮርፖሬሽኑ የስራ አመራር የጥገና ስራው ያለበትን ደረጃ በአካል ተገኝቶ በመመልከት የቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም የባቡር መስመር ፕሮጀክቱን ሃብትና ንብረት በመጠበቅና በግንባታ ስራውም የራሱን አሻራ በማሳረፍ  የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጅነር ብርሃኑ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ የፕሮጀክቱ ጥገና ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ መንግስት በተለየ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

የፕሮጀክቱ ጥገናም በቀጣይ የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነቃቃትና ለአገር እድገት መሰረት በመሆን  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ እንደሆነም አብራርተዋል።

አዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዳንኤል ኪዳነማሪያም በበኩላቸው የፕሮጀክቱ የጥገና ስራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ  አስረድተዋል።


 

ከአዋሽ -ኮምቦልቻ -ሃራ ገበያ 392 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ፕሮጀክት በአራት አቅጣጫ የጥገና ስራው እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው የካምፖች፣ የሀዲድ መስመርና የባቡር ጥገና እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ጠግኖ ለማስረከብ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በጉብኝቱ የኮርፖሬሽኑና የኮምቦልቻ ከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም