ለሀገራዊ ምክክሩ የተለዩት አጀንዳዎች ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጉልህ ድርሻ ያበረክታሉ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ የተለዩት አጀንዳዎች ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጉልህ ድርሻ ያበረክታሉ
ሐረር፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክሩ የተለዩት አጀንዳዎች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን በሐረር የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጋቸው ተከታታይ ውይይቶች፤ ለዘመናት የቆዩ መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ዋና ዋና አጀንዳዎችን ለይቶ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይህንኑ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔው የተለዩት አጀንዳዎች ወቅታዊና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሐረሪ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ዩሱፍ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከጥምረቱ ጋር በቅንጅት እየሠራ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሂደትም አበረታች ተግባራትን አከናውኗል።
ኮሚሽኑ የለያቸው አጀንዳዎች ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ለመገንባትና ለዘመናት ሳያግባቡ የቆዩ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሀገር ሽማግሌው አቶ መሀመድ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያሉ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሀገራዊ ምክክሩ ሚና ከፍተኛ ነው።
በመሆኑም ለዚህ ሂደት ስኬታማነት ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባናል ብለዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ የማያግባቡ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፤ ጠንካራ ሥርዓተ-መንግስት ለመገንባት፣ የጋራ ትርክትን ለማስረጽና ዴሞክራሲን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ አባገዳ አህመድ ዩስፍ ናቸው።
ኮሚሽኑ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው አጀንዳ በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ልዩነቶችን ወደ ትብብር በመቀየር ዘላቂ ሰላምን እንደሚያሰፍን ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልጸዋል።
በክልሉ የጀንኤላ ወረዳ የሰላም ቤተሰብ ሰብሳቢ መምህርት ሒሩት ታደሰ በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሀገሪቱ የነበሩ አለመግባባቶችን እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል በመውረድ ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር አድንቀዋል።
ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን ለይቶ ወደ ስራ መግባቱ ኢትዮጵያን ወደ አንድነት የሚያመጣ፣ ዘላቂ ሰላምን የሚያሰፍንና ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ታሪካዊ ዕድል በመጠቀም ሰላማዊና የተሻለች ሀገር ለመገንባት እያበረከቱ የሚገኘውን አስተዋጽኦ ይበልጥ እንደሚያጠናክሩም አክለው ገልጸዋል።