በከተማዋ ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው መናኸሪያ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው መናኸሪያ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር አስችሏል
ሚዛን አማን፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በሚዛን አማን ከተማ ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው አዲሱ መናኸሪያ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች ገለጹ።
በቅርቡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሚዛን አማን ከተማ የተገነባው አዲስ መናኸሪያ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወሳል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የመናኸሪያው ተገልጋዮች እንደገለፁት፤ አዲሱ መናኸሪያ ከዚህ ቀደም የነበረውን የመጥበብና የንጽህና ጉድለት ችግር በማስቀረት የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር አስችሏል።
ይህም መንግስት ሕዝብን ለእንግልት ይዳርጉ የነበሩ የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለይቶ በማዘመን ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል በዛብህ በቀለ እና አብዮት ወልደማርያም፤ ከዚህ ቀደም የነበረው መናኸሪያ ጠባብ በመሆኑ ቶሎ ስለሚሞላ አገልግሎት የሚሰጡበትን ተሽከርካሪ ውጭ ለማሳደር ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህም ለተሽከርካሪዎች ደህንነት ምቹ እንዳልነበር በማንሳት የእቃ መጥፋትና ለፓርኪንግ ወጪ የማውጣት ጫና ፈጥሮብን ቆይቷል አሁን ግን ይህ ችግር ተቀርፎልናል ብለዋል።
አዲሱ መናኸሪያ በአግባቡ ተጠብቆ እንዲዘልቅ የበኩላችንን ኃላፊነት እንወጣለን ብለዋል።
ከተሳፋሪዎች መካከል ወይዘሮ ዓለሚቱ ገረመው እና ታደለ ኃይለኢየሱስ፤ አዲሱ መናኸሪያ የተሻለ በመሆኑ ደህንነታቸው ተጠብቆ በሥነ ሥርዓት አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በዝናብ ጊዜ በሚፈጠረው ጭቃ ምክንያት ለመውጣትና መግባት እንኳ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው መንግስት ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ በማከናወን ለችግሩ መፍትሔ በመስጠቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘመዴ አንዳርጌ፤ በክልሉ የሚታዩ የመናኸሪያ አገልግሎት ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከ425 በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግደው የሚዛን አማን መናኸሪያ በውስጡ የትራንስፖርት ማኅበራት ቢሮ፣ የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት፤ ካፍቴሪያና ሌሎች ክፍሎችንም ያሟላ ነው ብለዋል።
ለግንባታው ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸው ለተሳፋሪዎች ምቹ ማረፊያና ሰፊ መንቀሳቀሻ እንዲኖረው ተደርጎ መሰራቱን ጠቁመዋል።
በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ መናኸሪያዎች በዲጂታል ሲስተም ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን በቅርቡ የተመረቀውን የታርጫና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የቦንጋ መናኸሪያዎች ለአብነት ጠቅሰዋል።