በቱሪዝም ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን በማፍራት የሀገርን ኢኮኖሚና ገጽታ ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በቱሪዝም ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን በማፍራት የሀገርን ኢኮኖሚና ገጽታ ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በቱሪዝም ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን በማፍራት የሀገርን ኢኮኖሚና ገጽታ ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፌደራል ቱሪዝም ኢንስቲትዩት “የላቀ ክህሎት ለቱሪዝም እድገት” በሚል መሪ ቃል 13ኛውን የቱሪዝምና የመስተንግዶ ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበር ጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፣ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ተዋናዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ መንግሥት በቱሪዝም ዘርፉ ውጤታማና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
ይህንን ማሻሻያ ተከትሎም የፌደራል ቱሪዝም ኢንስቲትዩትን የማጠናከር ሥራ የተሠራ ሲሆን፣ ተቋሙ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የቱሪዝም መስኮች ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉን ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ለበርካታ ዜጎች መድረስ መቻሉን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህም ለብዙዎች የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዘርፉ ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ሀገራት ገበያም ተወዳዳሪ መሆን የሚችል የሰው ኃይል እየፈራ ይገኛል፤ ይህ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ቱሪዝም ካለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባሻገር ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው በቀጣይም የአገልግሎት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ በልዩ ትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
የቱሪዝምና መስተንግዶ ሳምንት መከበሩ፣ የሥራ ገበያውንና የሰለጠነውን የሰው ኃይል በቀጥታ ለማገናኘት እንዲሁም ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዱ ጠቃሚ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የፌደራል ቱሪዝም ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎችን በማፍራት ለኢንዱስትሪው ዕድገት የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝና በቀጣይም ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የዘንድሮው የቱሪዝምና መስተንግዶ ሳምንትም ኢንስቲትዩቱን ይበልጥ ውጤታማ ሊያደርጉ በሚችሉና ዘርፉን በሚያሳድጉ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር ገልጸዋል።