ቀጥታ፡

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የሀገርን ዕድገትና ብልፅግና የሚያፋጥኑ ተግባራት ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሰረት የሚመሰረተው አዲስ መንግሥት የሀገርን ዕድገትና ብልፅግና ለሚያፋጥኑ የልማት ስራዎች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ብልፅግና ፓርቲ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምፅ አግኝቷል፡፡ 

በመሆኑም አሸናፊው ብልፅግና ፓርቲ በመጪው መስከረም ወር ላይ አዲስ መንግሥት የሚመሰርት ይሆናል፡፡

አዲስ የሚመሰረተውን መንግሥት በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን፥ አዲሱ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ አብሮነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የሀገር ዕድገትና ብልፅግናን የሚያፋጥኑ ተግባራትን በስኬት ማከናወን እንዳለበትም ነው ያነሱት።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የስነ መንግሥትና ሕዝብ አስተዳደር ተመራማሪና ተንታኝ ጫሊ ኢተፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ምርጫ ሕዝብ ድምፅ ለሰጠው ፓርቲ አደራና ኃላፊነት የሚያስረክብበት የዴሞክራሲ ሂደት ነው።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መካሄዱን ጠቅሰው፥ በምርጫው ውጤት መሰረት አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የተጀመሩ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ስራዎች ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

የትኛውም ሀገራዊ ችግር በምክክርና በውይይት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ በሆደ ሰፊነት መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ለመልካም አስተዳደርና ለሀገር እድገት ማነቆ የሆኑ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀሩ ፖሊሲዎችና አሰራሮችን በተደራጀ መልኩ መተግበር ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለጎረቤት በሚል መርህ እየተከተለች ያለው ቀጣናዊ ትስስርን የማጠናከር የመሪነት ሚናዋን ማስቀጠልም አለበት ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህርና ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በቀጣይ የሚመሰረተው መንግሥት  የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ዘርፉን ይበልጥ በማዘመን ብልሹ አሠራርን ማስቀረት ቀዳሚ የቤት ሥራው ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

ለዚህም የተጀመረው የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና የሉዓላዊነት ቁልፍ አጀንዳ የሆነውን በምግብ ራስን የመቻል ግብን የሚያረጋግጡ የፖሊሲ ትግበራዎችን ማጠናከር ከአዲሱ መንግሥት የሚጠበቁ ሥራዎች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም