ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን ለስርዓተ ጾታ እኩልነት ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን ለስርዓተ ጾታ እኩልነት ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ስፖርት (IMS) ጋር በመተባበር፤ በስርዓተ ጾታ እና የሴት ጋዜጠኞችን ማብቃት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እያካሄደ ይገኛል። 


 

በዚህ መድረክ ላይ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች የተወጣጡ ሴት ጋዜጠኞች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

ዋና ዳይሬክተሯ ሃይማኖት በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙኃን የስርዓተ ጾታ እኩልነት ለማስፈን ለሚከናወኑ ተግባራት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል። 

በተለይም ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ጉልህ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በአመራርነትና በውሳኔ ሰጪነት ደረጃ ሊጎለብት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ሴቶች የሕብረተሰቡ ግማሽ አካል እንደመሆናቸው መጠን እንደ የዕድሜያቸውና እንደ የስርዓተ-ፆታ ፍላጎታቸዉ፣ ተግዳሮቶቻቸውንና እምቅ አቅማቸዉን የሚመጥኑ ፕሮግራሞች ሊዘጋጁላቸው እንደሚገባ ይደነግጋል ብለዋል።

ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ ንቁ ተጠቃሚና ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ የሚያስገድዱ ጠንካራ መርሆዎች መኖር እንዳለባቸውም በአዋጁ መደንገጉን ጠቅሰዋል፡፡

በማንኛውም የመገናኛ ብዙኃን ውጤት ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን፤ የሴቶችን ክብርና እኩልነት የመጠበቅ የሕግ ግዴታም መጣሉን ነው የገለጹት፡፡ 

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ ደረጃ የሴቶችን መብት፣ ውክልናና ተሳትፎ ለማጠናከር በርካታ ስምምነቶችን ተቀብላ እየተገበረች መሆኑን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በብዙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ውስጥ በአመራር ደረጃ፣ በውሳኔ ሰጪነት እና በይዘት ዝግጅት ሂደት ላይ የሴቶች ተሳትፎ መሻሻሎችን እያሳየ ቢሆንም ይበልጥ ሊጎለብት ይገባል ብለዋል፡፡ 


 

ይህንን ለማቃለል በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ውስጥ ጠንካራ የስርዓተ ጾታ ምላሽ ሰጪ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲዎችን፣ የሴት ባለሙያዎችን የሥራ አካባቢ ደህንነት የሚያረጋግጡ መመሪያዎችን እና ግልጽ የክትትልና የተጠያቂነት አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። 

በቀጣይም የሴቶችን ተሳትፎና አመራር ሰጪነት ማጠናከር፣ በይዘት ምርትና ስርጭት ሂደት የስርዓተ ጾታ ሚዛንን ማረጋገጥ፣ ከፆታዊ ትንኮሳ ነፃ የሆነ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር፣ የሚዲያ ይዘቶችን በስርዓተ ጾታ መነፅር መከታተል፣ አግላይና አድሎአዊ የሆኑ ቋንቋዎችን ማስወገድ፣ ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታና ሥልጠና ሥርዓት ማበጀት ይገባል ብለዋል። 

መገናኛ ብዙኃን የተጠናከረ የስርዓተ ፆታ ኤዲቶሪያል አሰራር በመዘርጋት፣ ለስርዓተ ፆታ ጉዳዮች በቂ የአየር ሰዓትና ሽፋን በመስጠት፣ ሕግና የሙያውን ሥነ-ምግባር አክብረው የሚያቀርቡበትን አሠራር መዘርጋት ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ በአጽንኦት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም