ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎችን በማራባት ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያከፋፈለ ነው

አምቦ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያ በማራባት የአካባቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጉደር ማሞ መዘመር ካምፓስ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አማን ሪቂቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ተግባሩ ጎን ለጎን፣  በምርምር በማስደገፍ የተሻሻሉ የወተት ላሞችን በማራባት ለአካባቢው አርሶ አደሮች እንዲደርሱ እያደረገ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ከቶኬ ኩታዬ ወረዳ ጋር በመቀናጀት፣ ድጋፍ የሚገባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች በመለየት የወተት ላሞቹ የሚቀርቡበትን ሁኔታ በማመቻቸት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ይህም የአርሶ አደሮቹን ገቢ ከመጨመር ባለፈ፣ በአካባቢው የወተትና የወተት ተዋጽኦ በሰፊው ለገበያ እንዲቀርብ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ 15 ዝርያቸው የተሻሻለ የወተት ላሞች ለአካባቢው አርሶ አደሮች መስጠቱን ተናግረዋል።

በካምፓሱ የወተት ከብት እርባታ ምርምር ቡድን መሪ አቶ ተሬሳ ተመስገን በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን የወተት ምርት ለማሳደግ የሆሮ፣ ቦረና እና የውጪ አገር ዝርያ ያላቸው ላሞች ዝርያን በምርምር በማዳቀልና በማራባት የአካባቢው አርሶ አደሮች እያከፋፈለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በምርምር ዝርያቸው የተሻሻሉ 170 የወተት ላሞች እንደሚገኙ አንስተው፤ ከእነዚህም መካከል በዘንድሮው ዓመት 10 የሚሆኑትን ለአርሶ አደሮች ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በምዕራብ ሸዋ ዞን የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶ አደር ምስጋና ለታ እንደተናገሩት፤ ከዩኒቨርሲቲው ከተሰጣቸው የወተት ላም በቀን እስከ 15 ሊትር ወተት እያገኙ ነው።

የወተት ምርቱን ለአካባቢው ሕብረተሰብ በማቅረብ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን በጥሩ ሁኔታ እያስተዳደሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም