ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሮቤ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት ይበልጥ እንደሚጠናከሩ የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር «የትራፊክ አደጋን በጋራ እንከላከል» በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው የትራፊክ ሳምንት በባሌ ሮቤ ከተማ ተከብሯል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ከማል ማሜ እንዳሉት፤ በክልሉ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።


 

በተለይም የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ቁጥጥርን በማጠናከርና ግንዛቤን በማሳደግ፣ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በባሌ ሮቤ የተከበረው የትራፊክ ሳምንት ኅብረተሰቡ በትራፊክ ሕግ እና ደንብ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል በክረምቱ ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የትራፊክ ደህንነትና ግንዛቤ መፍጠር አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌደራል የመንገድ ደህንነት እና መድህን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሐሰን በበኩላቸው፤ የትራንስፖርት ዘርፉ ሀገሪቱ ለተያያዘችው የለውጥ ሂደት ስኬታማነት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስታውሰዋል።


 

ይሁን እንጂ ለትራፊክ ደህንነት መረጋገጥ የተቀናጀ አሠራር ባለመዘርጋቱ አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ይህም በዜጎች ላይ የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ከማስከተሉም በላይ፣ በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በተገነቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ35 ሺህ በላይ የትራፊክ አደጋዎች መድረሳቸውንና በአደጋውም የ2 ሺህ 800 ዜጎች ሕይወት ማለፉን የገለጹት አቶ መሐመድ፤ ይህም የችግሩን አሳሳቢነት በግልጽ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልም የሕግ ማዕቀፎችንና የተሽከርካሪ ደረጃዎችን ማሻሻል፣ የትራፊክ ቁጥጥር ሂደትን ማዘመን፣ ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ የተጀመሩና ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሥራዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኃይሌ በበኩላቸው፤ የትራፊክ ሳምንት መከበሩ የኅብረተሰቡን የትራፊክ ግንዛቤ ለማጎልበትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል።


 

የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ዲኖ አሚን ደግሞ በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘው የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ፣ የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ አደጋን ለመቀነስ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሐግብሩ ማጠቃለያ ላይ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሌሎች ዜጎችን የማሰብ ሥነ ሥርዓት በሻማ ማብራትና የእግር ጉዞ ተከናውኗል።

በዝግጅቱ ላይ በከተማዋ የሚገኙ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት፣ የባጃጅ ተሽከርካሪ ማኅበራት፣ ነዋሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም