ቀጥታ፡

በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በፍራፍሬ ልማት ላይ በመሳተፍ ውጤታማ ሆነናል

ባህር ዳር፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በፍራፍሬ ልማት ላይ በመሳተፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን አሳድገናል ሲሉ በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።

በክልሉ በክረምት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩም ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በማዘጋጀትና አርሶ አደሩን ተሳታፊ በማድረግ ከ261 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን ለመሸፈን እየተሰራ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላው ለአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለደን ልማት፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትና መሰል ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተው ተከላ እየተከናወነ ይገኛል።

በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ አንጉቲ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ምንይችል ወንድሜነህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በብዙ ነገር ጠቅሞናል ብለዋል።

በተለይም በአካባቢው በስፋት እየተካሄደ ባለው የክላስተር አቮካዶ ልማት ከምርት ሽያጭ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውም ገልፀዋል።

ቀደም ሲል በአካባቢው ጤፍ፣ ዳጉሳና በቆሎ በስፋት ይመረት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ አብዛኛው አርሶ አደር አቮካዶ እያለማ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካሳሁን አበበ በበኩላቸው፤ የአቮካዶ ልማት ከሌሎች ሰብሎች በተሻለ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።

የክላስተር የአቮካዶ ልማት አርሶ አደሩ እርስ በእርሱ እንዲረዳዳ ከማድረጉም በላይ የግብይት ሰንሰለቱን የተሳለጠ እንዳደረገው ተናግረዋል።

ቀጣይም በአረንጓዴ ልማት የደን ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ ባሻገር የጀመሩትን የአቮካዶ ልማት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለመጀመሪያ ጊዜ በአቮካዶ ልማት ላይ መሳተፋቸውን የገለፁት ደግሞ የጥሩ ብርሃን ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አየሁ ሙሉ ናቸው። 

ከመጋቢት ወር ጀምረው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ከሰሞኑ በክላስተር ተደራጅተው ማልማት መጀመራቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ በክረምት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ25 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የቡናና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች ተዘጋጅተው ተከላ እየተከናወነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም