ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በአጠቃላይ 100 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ

ባህርዳር ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በአጠቃላይ 100 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ የተጀመረውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና  በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ ጥላሁን ወርቅነህ የፈተናውን አጀማመር አስመልክተው እንደገለጹት፤ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና በአጠቃላይ በ6 ዙር 100 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን ለማስፈተን እየተሰራ ነው።


 

በዛሬው እለት እየተሰጠ ባለው የመጀመሪያው ዙር ፈተናም በ23 ማዕከላት ተማሪዎችን ለማስፈተን የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ከተፈታኞች መካከልም 60 በመቶ የሚሆኑት በኦንላይን (በበይነ መረብ) ፈተናቸውን የሚወስዱ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የፈተናው አሰጣጥም ዘመኑን የዋጀና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ያሳደገ ከመሆኑም በላይ ኩረጃን በማስቀረት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ፈተናው ያለምንም የቴክኒክ ችግር እንዲጠናቀቅ የትራንስፖርት፣ የኃይል አቅርቦትና የጸጥታ ዘርፎች በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

የመብራት መቆራረጥም  እንዳያጋጥም የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው ለዚህም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

ተማሪዎች ያለምንም የሥነ ልቦና ጫና ፈተናቸውን እንዲፈተኑ ሰፊ የሞራል ግንባታ ስራ ቀድሞ መከናወኑን ጠቁመው ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎችና የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ማህበረሰቡም ለፈተናው ስኬት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።

በአጠቃላይ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በክልሉ በከፍተኛ የዝግጅት መንፈስ በስኬት መጀመሩን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም