አዲስ የሚዋቀረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረውን የብልፅግና ጉዞ የማስቀጠል የህዝብ አደራ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የሚዋቀረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረውን የብልፅግና ጉዞ የማስቀጠል የህዝብ አደራ አለበት
አዲስ አበባ፤ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሰረት የሚዋቀረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ የፈጠረውን የብልፅግና ጉዞ የማስቀጠል የህዝብ አደራ እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ እንደሚመረጡ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ-54 ላይ በግልፅ ተመላክቷል።
የምክር ቤቱ አባላትም የመላው ሕዝብ ተወካዮች በመሆናቸው ተገዥነታቸው ለሕገ-መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናቸው ብቻ መሆኑን በሕዝብ ውክልና የክትትልና ቁጥጥር ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተቀምጧል።
በሕገ-መንግሥት አንቀፅ-58 መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑም ከማብቃቱ አንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል።
ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የተካሄደውን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎም በመጪው መስከረም ወር አሸናፊው የብልፅግና ፓርቲ አዲስ መንግሥት እንደሚመሰርት ይጠበቃል።
ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመንም በዚህ ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ በመጪው መስከረም አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቋቋም ይሆናል።
በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጀ እንዳሉት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎችን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጽኑ ፍላጎት አስመስክሯል።
ሕብረተሰቡ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ጭምር በመሰለፍ ይወክለኛል ለሚለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ መስጠቱም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
በጠቅላላ ምርጫው ውጤት መሰረት የሚዋቀረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ የፈጠረውን የብልፅግና ጉዞ የማስቀጠል የህዝብ አደራ እንዳለበት ተናግረዋል።
በቀጣይ መስከረም በይፋ ሥራውን የሚጀምረው አዲሱ ምክር ቤትም የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች የሚያፋጥን ጥብቅ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንደሚጠበቅበት አንስተዋል።
በተለይም ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች በስኬት ተጠናቀው የሀገርና ህዝብ ሁለንተናዊ የዕድገት አቅም እንዲሆኑ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
በምክር ቤቱ የጤና፣ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በርካታ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።
አዲሱ ምክር ቤትም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ የሚያስችል ጥብቅ የልማት ፕሮጀክት አፈፃጸም የክትትልና ቁጥጥር ሥራን የመወጣት የህዝብ አደራ እንደተሰጠው ገልጸዋል።
መንግሥት በፖሊሲ እርምጃና ውጤታማነት፤ ዜጎች ደግሞ በተባባሪነት ጠንካራ የትብብር ቁርኝት በመገንባት የኢትዮጵያን ዕድገት ማፋጠን እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
ዜጎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀገርን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዳስመሰከሩ ተናግረዋል።
በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ፤ በምርጫ ማግስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክርን ወደ ትብብር በማላቅ ለጠንካራ ዴሞክራሲና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ህብረተሰቡ መንግሥትን የማፅናት፤መንግስትም ለህዝብ የገባውን ቃል በመፈጸም ውጤታማ የዕድገት አቅም የሆኑ የልማት ሥራዎችን መገንባት እንዳለበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ብልፅግናና ዕድገት ለማረጋገጥና ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የልማት ግቦችን ለማሳካትና ኢትዮጵያን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ምክር ቤቱ የልማት ግቦችን ከግብ ሊያደርሱ የሚችሉ ሕጎችን የማውጣት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች በስኬት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ባለው ዕውቀት፣ጉልበትና አቅም ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የኢትዮጵያን እድገት ለማፋጠን የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።