ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራዊ እርምጃዎቿን አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራዊ እርምጃዎቿን አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራዊ እርምጃዎቿን አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ያሳተፈው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በእንጦጦ ፓርክ በተካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የየሀገራቱ አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ለዓለም ምሳሌ በሚሆን መልኩ በውጤታማነት እየተገበረች ትገኛለች።
መርሃ ግብሩ የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግ ባለፈ፣ በስራ ዕድል ፈጠራና ዘላቂ ልማትን እውን በማድረግ ረገድ ተጠቃሽ ውጤቶች እያመጣ መሆኑንም አብራርተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ የአረንጓዴ አሻራ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ረገድ የምትጫወተውን ግንባር ቀደም ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ አንድ ሀገር ብቻውን መፍትሔ ሊሰጠው የሚችለው ጉዳይ ባለመሆኑ በጋራ መስራት ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የዛሬው የችግኝ ተከላም ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ወሳኝ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለዱር እንስሳት ህልውና ዓይነተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ዛሬ የምንተክለው ችግኝ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ተስፋም ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል።