ቀጥታ፡

የመሬት አካውንት መግለጫና የተፈጥሮ ካፒታል አካውንት ፍኖተ-ካርታ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው፣ አካታችና የማይበገር ዕድገት ለማስመዝገብ ለምታደርገው ጥረት ጠቃሚ መሰረት ሆኖ የሚያገለግለው የመሬት አካውንት መግለጫና የተፈጥሮ ካፒታል አካውንት ፍኖተ-ካርታ ይፋ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዕትም የመሬት አካውንት መግለጫ ሪፖርት እና የተፈጥሮ ካፒታል አካውንት ፍኖተ-ካርታን ይፋ የማድረጊያ መርሃ ግብር እያካሄደ ይገኛል። 

በዚህ ይፋዊ መድረክ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረከት ፍስሃፅዮን፣ የዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማናጀር ጁልያን ቪክቶር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረከት ፍሰሃፅዮን በመድረኩ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ይፋ የሆኑት ሰነዶች ሀገራዊ የጋራ ራዕይን እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም አላቸው። 

በተለይም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመቅረጽ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል፣ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በጋራ ለመስራት ያለንን ቁርጠኝነት የምናሳይበት ነው ብለዋል።


 

እነዚህ ሰነዶች ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት በተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች የተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም የላቀ የትብብር ውጤት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰነዶቹ የተዘጋጁት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር በሚመራው ስቲሪንግ ኮሚቴ፣ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ተቋማት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሆነም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአህጉሪቱ  ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የቻለች ብሎም የሚጨበጥ ስኬት ያስመዘገበች ሀገር መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ያስመዘገበችው ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት በተጨባጭ መለወጡን ጠቁመዋል።

ለዚህ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ስኬት ለመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ለጤና እና ለትምህርት የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና በሌሎችም የተደረገው ኢንቨስትመንት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷልም ብለዋል። 

ቀጣይነት ያለውን ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማልማት ተግባራትም በተሳካ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም