ቡናን በጥራት በማምረት በዓመቱ የታቀደውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቡናን በጥራት በማምረት በዓመቱ የታቀደውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ነው
ሃዋሳ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ቡናን በጥራት በማምረት በዓመቱ የታቀደውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ ከቡና ገዢ ደንበኞቿ በተጨማሪ ከ20 በላይ አዳዲስ የዓለም ገበያዎችን መቀላቀሏ ይታወቃል።
ከኢትዮጵያ ቡና በዋነኝነት በመግዛት ቻይና የምትጠቀስ ሲሆን ካለፈው ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ቡናን በመግዛት ከነበረችበት 33ኛ ደረጃ ተስፈንጥራ በአሁኑ ወቅት 4ተኛዋ ቡና ገዢ ሀገር ሆናለች።
ባለፈው ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ከ35 ሺህ ቶን በላይ ቡና መላኳን መረጃዎች ያሳያሉ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፤ በቡና ዘርፍ ለውጥ የሚያመጡ አዳዲስ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡
በዚህም በየዓመቱ ለአለም ገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርትና ጥራት በመጨመር ገቢውን ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
በተያዘው 2018 በጀት ዓመትም ከ600 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለአለም ገበያ በማቅረብ 3 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዘንድሮ የአለም የቡና ዋጋ 40 በመቶ መቀነሱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በዓመቱ የተያዘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳካት ጥራትን መሰረት ያደረገ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እስካሁንም ከ400 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለአለም ገበያ መቅረቡን ጠቅሰው በዓመቱ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ የድህረ ምርት ጥራት አጠባበቅ ላይ በተሰራው ሰፊ ስራ በአለም ገበያ የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነት መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
የቡናን ጥራትና ምርታማነት የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበርና በክልሎች ያሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት በቀጣይም ዘርፉ በኢኮኖሚው ላይ እየተጫወተ ያለውን ሚና የማሳደግ ስራ በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፋን ቃሬ በበኩላቸው፤ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ26 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገ ጥረትም 24 ሺህ 100 ቶን ቡና ለማእከላዊ ገበያ መቅረቡን አስረድተዋል።
አለም አቀፍ የቡና ዋጋ መቀነስና ሌሎች ጉዳዮችን በምክንያት አንስተው እንደ ሃገር በጥራት በመወዳደር በእቅዱ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የቡና ጥራት ማሻሻያ ፓኬጆች አተገባበርን በማጠናከር የቡና ጥራትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር በትኩረት እንደሚከናወንም አመልክተዋል።