በሀገር አቀፍ ደረጃ 563 ሺህ 501 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ 563 ሺህ 501 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ 563 ሺህ 501 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በአብርሆት ቤተመጸሐፍት ተገኝተው የፈተናውን ሂደት አስጀምረዋል።
የፈተናውን ሂደት አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኅን በሰጡት መግለጫም፤ ፈተናው በበይነመረብና በወረቀት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሚወስዱት አጠቃላይ ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ 62 በመቶ የሚሆኑ በበይነ መረብ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በወረቀት እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ የማጠናከሪያ ትምህርት በመሰጠቱ ከፍ ያለ ውጤት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የዘንድሮው ፈተና ያለምንም ሥርቆት ተማሪዎች በችሎታቸውና በብቃታቸው የሚፈተኑት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ 563 ሺህ 501 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱም አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፤ በከተማዋ 58 ሺህ 309 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባም የመልቀቂያ ፈተናው በአጠቃላይ ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።