ቀጥታ፡

በደቡብ ኦሞ ዞን ለምግብነት እና ለገቢ ምንጭነት የሚውሉ ችግኞች በስፋት ይተከላሉ  

ጂንካ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኦሞ ዞን በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ለምግብነት እና ለገቢ ምንጭነት የሚውሉ ችግኞች በስፋት እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላርገው አዲሱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል።  

በዚህም ለምግብነት እና ለገቢ ምንጭነት የሚውሉ ችግኞች በስፋት እንደሚተከሉ የተናገሩት ኃላፊው፤ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በዋናነት ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ሞሪንጋ፣ አቮካዶ እንዲሁም ቡና በስፋት እንደሚተከል ገልጸዋል።

በተራቆቱ አካባቢዎች ላይ የሚተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁና አካባቢውም እንዲያገግም የችግኝ እንክብካቤ ሥራው በስፋት እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። 

እንደ ኃላፊው ገለጻ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከችግኝ ተከላ ባሻገር በአርብቶ አደር አካባቢዎች ህብረተሰቡን በማስተባበር የግጦሽ ሣር ከለላ እና የእንክብካቤ ሥራዎች በስፋት ይከናወናሉ።

መርሃ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም የመንግስት ሠራተኞችን ጨምሮ ከ100 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ ታቅዷል ብለዋል።


 

በዞኑ ማሌ ወረዳ በነታ ጫሊቲ ቀበሌ የሚኖሩት አርብቶ አደር እዮኤል ጋልሻ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በአካባቢው ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የተጎዱ አካባቢዎች ጭምር አገግመው ምርት መስጠት ጀምረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ በየዓመቱ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በችግኝ እንክብካቤ ሥራ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በወረዳው የአሸከር ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር ናስር ዶቄ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ቡና እና ሞሪንግ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።


 

ከግብርና ባለሙያዎች የተሻለ ምርት የሚሰጡ ችግኞችን መውሰዳቸውን እና ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዞኑ ሐመር ወረዳ የቡስካ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገሌ ዳሎ፤ በአካባቢው የቡስካ ተፈጥሯዊ ጥብቅ ደንን ከጉዳት ከመጠበቅ ባለፈ በአካባቢው ችግኝ በመትከል ሲንከባከቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም የተጎዱ አካባቢዎችን በአረንጓዴ ለማልማት በሚሰሩ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም