የዓለም ዋንጫ 3ኛ ቀን የጥሎ ማለፍ መርሐ-ግብር፤ ኮትዲቯር ከኖርዌይ፣ ፈረንሳይ ከስዊድን እና ሜክሲኮ ከኢኳዶር - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ዋንጫ 3ኛ ቀን የጥሎ ማለፍ መርሐ-ግብር፤ ኮትዲቯር ከኖርዌይ፣ ፈረንሳይ ከስዊድን እና ሜክሲኮ ከኢኳዶር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
ኮትዲቯር ከኖርዌይ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በዳላስ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በምድብ አምስት በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ኮትዲቯር በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።
ኖርዌይ በምድብ ዘጠኝ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
የሰሜን አውሮፓዊቷ ሀገር ወደ ጥሎ ማለፉ ስትገባ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሀገራቱ አሸናፊ በቀጣይ ዙር ከብራዚል ጋር ይጫወታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ፈረንሳይ ከስዊድን ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ በኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ፈረንሳይ በምድብ ዘጠኝ ሁሉንም ጨዋታዎቿን በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ በመሪነት አጠናቃለች።
ፈረንሳይ ወደ ጥሎ ማለፉ ስትገባ የአሁኑ ለ11ኛ ጊዜ ነው።
ተጋጣሚዋ ስዊድን በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ በምርጥ ሶስተኝነት ወደ 32 ዙር ገብታለች።
በውድድሩ ተሳትፎ ታሪኳ ለጥሎ ማለፍ ስታልፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ።
አሸናፊው ቡድን በቀጣዩ ዙር ከፓራጓይ ጋር ይገናኛል።
ከዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሜክሲኮ ከኢኳዶር ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በሜክሲኮ ሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሜክሲኮ በምድብ አንድ በዘጠኝ ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን በውድድሩ ተሳትፎዋ ታሪክ ለ10ኛ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።
ተጋጣሚዋ ኢኳዶር በምድብ አምስት አራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ በምርጥ ሶስተኝነት ወደ ጥሎ ማለፍ ገብታለች።
ሁለቱ ቡድኖች በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ጃፓን እና ኮሪያ ሪፐብሊክ እ.አ.አ በ2002 በጣምራ ባዘጋጁት 17ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በምድብ መርሐ ግብር ተገናኝተው ሜክሲኮ 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ሀገራቱ ከ24 ዓመታት በኋላ በጥሎ ማለፉ ተገናኝተዋል።
ሜክሲኮ ወደ ጥሎ ማለፍ ስትሸጋገር ለ10ኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ተጋጣሚዋ ኢኳዶር ጥሎ ማለፍ ስትገባ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የዛሬው ጨዋታ አሸናፊ 16 ውስጥ ከእንግሊዝ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።