ብራዚል ጃፓንን በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቀለች - ኢዜአ አማርኛ
ብራዚል ጃፓንን በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቀለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ32ቱ የጥሎ ማለፍ ሁለተኛ መርሐ ግብር ብራዚል ጃፓንን 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ማምሻውን በሂውስተን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ካይሾ ሳኖ በ29ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ባስቆጠረው ግሩም ጎል ጃፓን መሪ ሆናለች።
ከእረፍት መልስ ካሲሚሮ በ56ኛው ደቂቃ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ ላይ ያሳረፈው ግብ ብራዚልን አቻ አድርጓል።
ተቀይሮ የገባው ጋብርኤል ማርቲኔሊ በ95ኛው ደቂቃ ለብራዚል የማሸነፊያውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ብራዚል በኳስ ቁጥጥር እና ግልጽ የግብ እድሎችን በመፍጠር ተሽላ ተገኝታለች።
ውጤቱን ተከትሎ የአምስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ብራዚል 16 ውስጥ ገብታለች።
ብራዚል በቀጣዩ ዙር ከኮትዲቯር እና ኖርዌይ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።
የጃፓን የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ጉዞ 32ት ውስጥ ተገቷል። የእስያዋ ጃፓን እስከ አሁን ብራዚልን አሸንፋ አታውቅም።