የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን ከወርቅ ንግድ ወደ ትግራይ ወጣቶች ሽያጭ ተሸጋግሯል - የወለዶ ትግራይ ፖለቲካ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጉዕሽ ግደይ - ኢዜአ አማርኛ
የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን ከወርቅ ንግድ ወደ ትግራይ ወጣቶች ሽያጭ ተሸጋግሯል - የወለዶ ትግራይ ፖለቲካ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጉዕሽ ግደይ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን ከወርቅ ንግድ ወደ ትግራይ ወጣቶች ሽያጭ መሸጋገሩን የወለዶ ትግራይ ፖለቲካ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጉዕሽ ግደይ ገለጹ።
የወለዶ ትግራይ ፖለቲካ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጉዕሽ ግደይ በወቅታዊ የትግራይ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በዚህም የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በማፍረስና ከውጭ ጠላቶች ጋር በመተባበር ጦርነት ለመጫር በትግራይ ክልል ሁሉንም ፖለቲካዊና ሰላማዊ መንገዶች ዘግቶ በጉልበት የሚያስተዳድርበትን ሁኔታ ፈጥሮ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለትግራይ ህዝብ ሰላም የፈጠረ ታሪካዊ ስምምነት እንደነበር አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ ያለ ጦርነትና ሁከት መኖር የማይችለው የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን ግን ስምምነቱን በተግባር ማፍረሱን ጠቁመዋል።
የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እየተከታተለውና እያወገዘው እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ለዚህም የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ መንግስት ያወጧቸውን መግለጫዎች በማሳያነት አንስተዋል።
የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር "ፅምዶ" በሚል ስያሜ እያደረገ ያለው ህገወጥ እንቅስቃሴ የሀገር ክህደት፣ ከህገ-መንግስቱና ከትግራይ ህዝብ ጥቅም አኳያ በተጻራሪ የቆመ ነው ብለዋል።
ቡድኑ ሲፈጠር ጀምሮ ለኢትዮጵያ ብሎም ለትግራይ ህዝብ ጥቅም ከመታገል ይልቅ ለኤርትራ መንግስት ጥቅም የታገለበት እንደሚበልጥም አስረድተዋል።
የትግራይ ህዝብ ቡድኑ በመራቸው ጦርነቶች ሁሉ ምንም ዓይነት ጥቅም እንዳላገኘ የተናገሩት አቶ ጉዕሽ፤ ይህ የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን አሁንም በተደጋጋሚ በወደቀበት መንገድ እየተጓዘ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ጋር ተሰልፎ ለጦርነት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቡድኑ የትግራይ ወጣቶችን እያገተና ወላጆችንም እያሰረ ትውልድን ለማጥፋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ይህም መላው የትግራይ ህዝብ ከቡድኑ ጋር እንዳልሆነና በፈቃደኝነት እንደማይዋጋ ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን ከዚህ ቀደም ወርቅ ይሸጥ እንደነበር ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የትግራይ ወጣቶችን በመሸጥ የገቢ ምንጩ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ ከገባበት ቀውስ ለመታደግ ከፌዴራል መንግስት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ያሉት አቶ ጉዕሽ፤ ይህ ቡድን እንዲወገድ፣ የትግራይ ህዝብ ዘላቂ ሰላም እንዲያገኝና በቡድኑ ምክንያት ከጎረቤቶችና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የተፈጠረውን ቅሬታ ለመፍታት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የትግራይ ህዝብም ከኢትዮጵያ መንግስትና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጎን በመሆን ኋላቀሩን የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።
የፌዴራል መንግስትም የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን እስካሁን ለፈጸማቸው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች በትዕግስት፣ በተረጋጋና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ ቡድኑ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ወደ አደገኛ ደረጃ ስለተሸጋገረ የትግራይን ህዝብ ማዳንና የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር የሚያስችሉ ህገ-መንግስታዊና ፖለቲካዊ ስራዎችን መስራት አለበት ብለዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላም ለማደፍረስ እና ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሱ በሚገኙ የህወሓት ጽንፈኛ አመራር አባላት እና በቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን ይታወሳል።