የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ውበትና ድምቀት የሚያስደንቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ውበትና ድምቀት የሚያስደንቅ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ውበትና ድምቀት የሚያስደንቅ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፕሮጀክቱ መዲናዋን የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋም፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች እንዲሁም ዓለም አቀፍ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን ስልታዊ ሽግግር የሚያፋጥን ታላቅ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ 87 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት የሚሸፍንና 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከተማዋን ጽዱ ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎቿ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ባዘጋጀው የምስጋና መርሐ-ግብር ላይ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎችም ፕሮጀክቱን ጎብኝተዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ልማቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንና ለከተማዋ ውበት ተጨማሪ ድምቀት መፍጠሩን በአድናቆት ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ፈድሉ ኢብራሂም፤ የቀበና ወንዝ ቀደም ሲል ለረጅም ዘመናት በቆሻሻ መጣያነቱና በማይመች ሁኔታው ይታወቅ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የተከናወነው አስደናቂ የልማት ስራ ግን አካባቢውን በሚያስደንቅ ሁኔታ የቀየረው ሲሆን ይህም ትልቅ ደስታና እርካታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ስሙ በክፉ ይነሳ የነበረው ይህ አካባቢ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ውብ መልክዓ ምድር መቀየሩ እንዳስደነቃት የተናገረችው ደግሞ እስራኤል አሸናፊ ናት።
በአሁኑ ወቅት ስፍራው ለህጻናትና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ምቹ መጫወቻና የመዝናኛ ቦታ ሆኖ መዘጋጀቱ እንዳስደሰታት ተናግራለች።
ወጣት ዳንኤል በበኩሉ፤ የቀበና ወንዝ ዳርቻ ቀደም ሲል አስቀያሚና ለጤና ጠንቅ የነበረ ስፍራ መሆኑን አስታውሶ ይህን ስፍራ ውብ ያደረጉ አመራሮች ትልቅ ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግሯል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ከድር ጃርሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአካባቢው ላይ በአጭር ጊዜ የታየው ለውጥ እጅግ አስደናቂ እይታን መፍጠሩን አንስተዋል።
ይህ ስፍራ ቀደም ሲል በቆሻሻ ተሸፍኖ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በሐይቅ፣ በታንኳና በአረንጓዴ ሥፍራ የተዋበ መሆኑንና አካባቢው ለኑሮ ምቹና ማራኪ ሆኖ መገንባቱን የጠቀሱት ደግሞ መቅደስ በቀለ ናቸው።
አካባቢውን ለረጅም ዓመታት የሚያውቁት አቶ አብደላ ኑሪ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ስፍራው እጅግ ምቾት የማይሰጥና የሚያሳቅቅ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የታየው ውበትና ልማት እጅግ አስገራሚ መሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው፤ ይህ ተግባር ለመንግስት ትልቅ ምስጋና የሚያሰጥ ድንቅ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።