በክልሉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እየተጠናቀቁ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እየተጠናቀቁ ናቸው
ነቀምቴ ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የህብረተሰቡን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍና የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እየተጠናቀቁ መሆኑ ተገለጸ።
በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋዩ ቱቃ ወረዳ በ99 ሚሊየን ብር በላይ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በፕሮጀክት ምረቃ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ለሜሳ አየለ እንደገለፁት፤ መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍና የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው።
በዚህም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቁ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት ፕሮጀክቶችም የስራ እድል የሚፈጥሩና የዞኑን የገቢ አቅም የሚያሳድጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደሱ ለሚ በበኩላቸው፤ መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መስራቱን አንስተዋል።
ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ማስገባቱን ተናግረዋል።
ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉት ፕሮጀክቶች መካከል የስራ እድልን ማስፋት የሚያስችሉ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የምስራቅ ወለጋ ዞን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቃዱ ገመዳ በበኩላቸው፤ መንግስት ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የገባውን ቃል ለመፈጸም በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የዛሬዎቹ ፕሮጀክቶች ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የዋዩ ቱቃ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል መኮንን በበኩላቸው ፤ከ99 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የከብት እርባታ ማእከል ፣ ድልድዮች ፣ መንገዶች ፣ የቡሳ ጎኖፋ እህል ማከማቻ መጋዘን እና ሌሎች ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።
የልማት ፕሮጀክቶቹም ለማህበረሰቡ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡና የወረዳውን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደሚያሳልጡ ጠቁመዋል።